ሳምንት 10 · ቀን 46 (ሰኞ)
📅 Hidar 7, 2019
ኦሪት ዘኍልቍ 8, 9, 10, 11 · ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1
ኦሪት ዘኍልቍ
ምዕራፍ 8
የመብራቶቹ አቀማመጥ
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም በለው፤ ‘ሰባቱን መብራቶች በየቦታቸው በምታስቀምጥበት ጊዜ በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።’ ” 3.አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹ በመቅረዙ ላይ ሆነው ፊት ለፊት እንዲያበሩ አስቀመጣቸው። 4.የመቅረዙ አሠራር እንዲህ ነበር፤ ከመቆሚያው እስከ አበቦቹ ያለው ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ የመቅረዙም አሠራር እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው መሠረት ነበር።የሌዋውያን ለአገልግሎት መለየት
5.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6.“ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ በሥርዐቱ መሠረት አንጻቸው። 7.ስታነጻቸውም እንዲህ አድርግ፤ በሚያነጻ ውሃ እርጫቸው፤ ገላቸውን በሙሉ በምላጭ ተላጭተው ልብሳቸውን ይጠቡ፤ በዚህም ይንጹ። 8.በዘይት ከተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን ጋራ አንድ ወይፈን ይውሰዱ፤ ከዚያም ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን ሌላ ወይፈን አንተ ትወስዳለህ። 9.ሌዋውያኑን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አምጣ፤ መላውንም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሰብስብ፤ 10.ሌዋውያኑን በእግዚአብሔር ፊት አቅርብ፤ ከዚያም እስራኤላውያን እጃቸውን ይጫኑባቸው። 11.ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ያቅርባቸው። 12.“ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርባቸው። 13.ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር አቅርባቸው። 14.በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ። 15.“ሌዋውያኑን ካነጻሓቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሃቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤ 16.እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ። 17.ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብጽ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ። 18.በእስራኤል በተወለዱት ተባዕት በኵሮች ሁሉ ምትክም ሌዋውያኑን ወስጃለሁ። 19.እስራኤላውያንን ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት እንዲያከናውኑና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ቢቀርቡ እንዳይቀሠፉ ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፣ ከእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ሌዋውያኑን ስጦታ አድርጌ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ።” 20.ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በሌዋውያኑ አደረጉ። 21.ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም ዐጠቡ፤ ከዚያም አሮን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፤ እንዲነጹም ማስተስረያ አደረገላቸው። 22.ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር ሆነው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት ለማከናወን ገቡ። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አስፈላጊውን በሌዋውያኑ አደረጉ። 23.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24.“ሌዋውያንን የሚመለከተው ደንብ ይህ ነው፤ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ለመሳተፍ ሃያ ዐምስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች ይመጣሉ፤ 25.ዕድሜያቸው ዐምሳ ዓመት ሲሞላ ግን መደበኛ አገልግሎታቸውን ይተዉ፤ ዳግም ሥራ አይሥሩ። 26.ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው በመገናኛው ድንኳን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ያግዟቸዋል እንጂ ራሳቸው መሥራት የለባቸውም። ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የምታሰማራቸው በዚህ መልኩ ነው።”ምዕራፍ 9
የፋሲካ በዓል
1.ከግብጽ ምድር በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ምድረ በዳ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤ 2.“እስራኤላውያን በተወሰነው ጊዜ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ አድርግ፤ 3.በዓሉንም በዚህ ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በተወሰነው ሕግና ሥርዐት መሠረት ሁሉ አክብሩ።” 4.ስለዚህ ሙሴ ፋሲካን እንዲያከብሩ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ 5.እነርሱም በመጀመሪያው ወር፣ በዐሥራ አራተኛውም ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካ አደረጉ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉንም አደረጉ። 6.አንዳንዶቹ ግን የሰው ሬሳ በመንካታቸው በሥርዐቱ መሠረት ረክሰው ስለ ነበር በዚያ ዕለት የፋሲካን በዓል ማክበር አልቻሉም፤ ስለዚህም በዚያ ዕለት ወደ ሙሴና ወደ አሮን መጥተው፣ 7.ሙሴን፣ “በሬሳ ምክንያት ረክሰናል፤ ታዲያ የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ ሆነን በተወሰነው ጊዜ እንዳናቀርብ ለምን እንከለከላለን?” አሉት። 8.ሙሴም፣ “እግዚአብሔር ስለ እናንተ የሚያዝዘውን እስካውቅ ድረስ ጠብቁ” ሲል መለሰላቸው። 9.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10.“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከእናንተ ወይም ከዘሮቻችሁ ማንኛውም ሰው በሬሳ ምክንያት ቢረክስ ወይም ሩቅ መንገድ ቢሄድ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ማክበር ይችላል፤ 11.ይህንም በሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ አራተኛው ቀን ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ያክብሩ፤ የፋሲካውንም በግ፣ ከቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋራ ይብሉት። 12.እስኪነጋ ድረስ ከዚህ ምንም አያስተርፉ፤ ከዐጥንቱም ምንም አይስበሩ፤ ፋሲካን በሚያከብሩበት ጊዜ ሥርዐቱን በሙሉ መጠበቅ አለባቸው። 13.በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ የሆነ ወይም ሩቅ መንገድ ያልሄደ ሰው ፋሲካን ሳያከብር ቢቀር፣ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መሥዋዕት በተወሰነው ጊዜ አላቀረበምና ከወገኖቹ ፈጽሞ ይለይ፤ ያም ሰው የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል። 14.“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ለማክበር ቢፈልግ በሕጉና በሥርዐቱ መሠረት መፈጸም አለበት፤ ለመጻተኛውም ሆነ ለአገሬው ተወላጅ የሚኖራችሁ ሕግ አንድ ይሁን።’ ”ከማደሪያው በላይ የነበረው ደመና
15.ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር። 16.ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው። 17.ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጕዟቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤ 18.እስራኤላውያን ጕዞ የሚጀምሩትም ሆነ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ በሚቈይበት ጊዜ ሁሉ ከሰፈር አይንቀሳቀሱም ነበር። 19.ደመናው በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን ቢቈይም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቃሉ እንጂ ተነሥተው አይጓዙም። 20.አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈየው ለጥቂት ቀን ብቻ ነበር፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጕዞ ይጀምራሉ፤ 21.አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ይቈያል፤ ደመናው ንጋት ላይ ሲነሣም ጕዟቸውን ይጀምራሉ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ደመናው ከተነሣ ጕዞ ይጀምራሉ። 22.ደመናው በድንኳኑ ላይ ለሁለት ቀንም ይሁን ለወር ወይም ለዓመት ቢቈይ፣ እስራኤላውያን በሰፈር ይቈያሉ እንጂ ጕዟቸውን አይቀጥሉም። 23.በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዛሉ፤ እነርሱም በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።ምዕራፍ 10
የብር መለከቶች
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ከተቀጠቀጠ ብር ሁለት መለከት አብጅ፤ ማኅበረ ሰቡን ለመጥሪያና ከሰፈራቸው እንዲነሡም ለመቀስቀሻ አድርጋቸው። 3.ሁለቱ መለከቶች ሲነፉ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አንተ ዘንድ ይሰብሰብ፤ 4.ነገር ግን አንዱ መለከት ብቻ ከተነፋ አለቆች ማለት የእስራኤል ጐሣ መሪዎች አንተ ዘንድ ይሰብሰቡ፤ 5.መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ሲነፋ በስተምሥራቅ የሰፈሩት ነገዶች ጕዞ ይጀምሩ፤ 6.መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲነፋ በስተ ደቡብ የሰፈሩት ነገዶች ጕዞ ይጀምሩ፤ ከፍ ያለው ድምፅ ጕዞ ለመጀመር ምልክት ይሆናል። 7.ማኅበሩን ለመሰብሰብ መለከቶች ይነፉ፤ ነገር ግን ድምፁ አይጩኽ። 8.“መለከቶቹን ካህናቱ የአሮን ልጆች ይንፉ፤ ይህም ለእናንተና ለሚመጡት ትውልድ የዘላለም ሥርዐት ይሁን። 9.በገዛ ምድራችሁ በግፍ በመጣባችሁ ጠላት ላይ ስትዘምቱ መለከቶቹን ከፍ ባለ ድምፅ ንፉ፤ በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ትታሰባላችሁ፤ ከጠላታችሁም እጅ ትድናላችሁ። 10.እንዲሁም በደስታችሁ ቀናት ማለት በተደነገጉት በዓሎቻችሁና የወር መባቻ በዓል ስታከብሩ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በኅብረት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቱን ንፉ፤ እነዚህም በአምላካችሁ ፊት መታሰቢያ ይሆኑላችኋል። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”እስራኤላውያን ከሲና ተነሡ
11.በሁለተኛው ዓመት፣ ሁለተኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ። 12.ከዚያም እስራኤላውያን ከሲና ምድረ በዳ ተነሥተው ደመናው በፋራን ምድረ በዳ እስኪያርፍ ድረስ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ተጓዙ። 13.እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ተጓዙ። 14.በመጀመሪያ የይሁዳ ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር። 15.የይሳኮር ነገድ ሰራዊት አለቃም የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበር። 16.እንዲሁም የዛብሎን ነገድ ሰራዊት አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበር። 17.ከዚህ በኋላ ማደሪያው ተነቀለ፤ ድንኳኑን የተሸከሙት ጌርሶናውያንና ሜራሪያውያንም ጕዞ ጀመሩ። 18.ቀጥሎም የሮቤል ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበር። 19.የስምዖን ነገድ ሰራዊት አለቃም የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበር። 20.እንዲሁም የጋድ ነገድ ሰራዊት አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበር። 21.ከዚህ በኋላ ቀዓታውያን ንዋያተ ቅድሳቱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነርሱ ከመድረሳቸው በፊት ማደሪያው ተተክሎ ነበር። 22.ቀጥሎም የኤፍሬም ሰፈር ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ሆነው ተጓዙ፤ አለቃቸውም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበር። 23.እንዲሁም የምናሴ ነገድ ሰራዊት አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበር። 24.የብንያም ነገድ ሰራዊት አለቃም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበር። 25.በመጨረሻም የዳን ሰፈር ሰራዊት ለሁሉም ክፍሎች የኋላ ደጀን በመሆን በዐርማቸው ሥር ተጓዙ፤ አለቃቸውም የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበር። 26.እንዲሁም የአሴር ነገድ ሰራዊት አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበር። 27.እንዲሁም የንፍታሌም ነገድ ሰራዊት አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበር። 28.እንግዲህ የእስራኤል ሰራዊት የጕዞ አሰላለፍ ሥርዐት ይህ ነበር። 29.በዚህ ጊዜ ሙሴ የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን፣ “እነሆ፤ እግዚአብሔር፣ ‘እሰጣችኋለሁ’ ወዳለን ምድር ጕዞ ጀምረናል፤ በመልካም ሁኔታ ስለምናኖርህ ከእኛ ጋራ ሂድ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል በጎ ነገር ለማድረግ ቃል ገብቷልና አለው።” 30.እርሱም መልሶ፣ “ይህስ አይሆንም፤ አልሄድም፤ ወደ አገሬና ወደ ወገኖቼ ተመልሼ እሄዳለሁ” አለው። 31.ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ አትለየን፤ በምድር በዳ ውስጥ የት መስፈር እንደሚገባን አንተ ታውቃለህ፤ ዐይናችንም ትሆናለህ። 32.ከእኛ ጋራ ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛም እናደርግልሃለን።” 33.ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ ተነሥተው የሦስት ቀን መንገድ ተጓዙ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትም በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ የሚያርፉበትን ቦታ በመፈለግ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር። 34.ከሰፈራቸው በሚነሡበት ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን ከላያቸው ነበር። 35.ታቦቱ ለጕዞ በተነሣ ጊዜ ሁሉ ሙሴ፣“እግዚአብሔር ሆይ፤ ተነሥ!
ጠላቶችህ ይበተኑ፤
የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ”
ይል ነበር። 36.ባረፉ ጊዜም፣
“እግዚአብሔር ሆይ፤
በብዙ ሺሕ ወደሚቈጠሩት እስራኤላውያን ተመለስ” ይል ነበር።
ምዕራፍ 11
ከእግዚአብሔር የወረደ እሳት
1.በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ስለ ደረሰባቸው ችግር በእግዚአብሔር ላይ አጕረመረሙ፤ እግዚአብሔርም ማጕረምረማቸውን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት በመካከላቸው ነደደች፤ ከሰፈሩም ዳርቻ ጥቂቱን በላች። 2.ሕዝቡ ወደ ሙሴ ጮኸ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እሳቲቱም ጠፋች። 3.ከዚህ የተነሣም የቦታው ስም፣ “ተቤራ” ተባለ፤ የእግዚአብሔር እሳት በመካከላቸው ነድዳለችና።እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የላከላቸው ድርጭት
4.ድብልቁ ሕዝብ ሌላ ምግብ ጐመጀ፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ያጕረመርሙ ጀመር፤ “ምነው የምንበላው ሥጋ ባገኘን ኖሮ! 5.በግብጽ ያለ ምንም ዋጋ የበላነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኵርቱ ትዝ ይለናል። 6.አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቷል፤ ከዚህ መና በቀር የምናየው የለም!” 7.መናው እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ የሙጫ መልክ ነበረው። 8.ሕዝቡ ተዘዋውሮ በመልቀም በወፍጮ ከፈጨ ወይም በሙቀጫ ከወቀጠ በኋላ በምንቸት ይቀቅለው ወይም ይጋግረው ነበር፤ ጣዕሙም በወይራ ዘይት የተጋገረ ያህል ይጣፍጥ ነበር። 9.ጤዛው ሌሊት በሰፈር ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም እንዲሁ ይወርድ ነበር። 10.ሙሴ፣ ሕዝቡ ሁሉ በየቤተ ሰቡ፣ በየድንኳኑ ደጃፍ ሆኖ ሲያለቅስ ሰማ። እግዚአብሔርም እጅግ ተቈጣ፤ ሙሴም ተጨነቀ። 11.እርሱም እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “እንዲህ ያለውን መከራ በባሪያህ ላይ ለምን አመጣህ? ለምንስ በፊትህ ሞገስ አላገኘሁም? የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝስ ምን አስቀይሜህ ነው? 12.ይህን ሁሉ ሕዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድን ነው? 13.ለዚህ ሁሉ ሕዝብስ ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? ሁሉም ‘የምንበላው ሥጋ ስጠን’ እያሉ ያለቅሱብኛል። 14.እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችልም። 15.እንዲህስ ከምታደርገኝ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ አሁኑኑ ግደለኝ፤ የሚደርስብኝን ጥፋት አልይ።” 16.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋራ ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ። 17.ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል። 18.“ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብጽ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር ሰምቷል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ። 19.የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለዐምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤ 20.ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብጽ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ” 21.ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤ 22.ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?” 23.እግዚአብሔርም ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር ክንድ ይህን ያህል ዐጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት። 24.ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው። 25.ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም። 26.ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋራ ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ። 27.አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። 28.ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ። 29.ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ቀንተህ ነውን? የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤ 30.ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ። 31.በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው። 32.በዚያ ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግስቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። 33.ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ። 34.ሌላ ምግብ ለማግኘት የጐመጁትን ሰዎች በዚያ ስለ ቀበሯቸው የቦታው ስም “ቂብሮት ሃታአባ” ተባለ። 35.ሕዝቡም ከቂብሮት ሃታአባ ወደ ሐጼሮት ተጕዘው እዚያው ሰፈሩ።ወደ ቆላስይስ ሰዎች
ምዕራፍ 1
1.በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፤
2.በቈላስይስ ለሚኖሩ፣ በክርስቶስ ለሆኑ ቅዱሳንና ታማኝ ወንድሞች፤
ከአባታችን ከእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ከአባታችን ከእግዚአብሔር ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።