Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 9 · ቀን 45 (አርብ) 📅 Hidar 4, 2019

ኦሪት ዘኍልቍ 6, 7 · ወደ ዕብራውያን 13

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘኍልቍ

ምዕራፍ 6

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2.ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥ 3.ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ። 4.ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ። 5.ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል። 6.ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። 7.ለአምላኩ ያደረገው እስለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው። 8.ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 9.ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው። 10.በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 11.ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል። 12.ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል። 13.የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤ 14.ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥ 15.አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ። 16.ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል። 17.አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል። 18.ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል። 19.ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤ 20.ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል። 21.ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል። 22.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23.ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው። 24.እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤ 25.እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤ 26.እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ። 27.እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።

ምዕራፍ 7

1.እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ማደሪያውን ፈጽሞ ከተከለ በኋላ፥ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ ከቀባና ከቀደሰ በኋላ፤ 2.የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ እነዚህም ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙ የነገዶች አለቆች ነበሩ። 3.መባቸውንም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፥ የተከደኑ ስድስት ሰረገሎች አሥራ ሁለትም በሬዎች፤ በየሁለቱም አለቆች አንድ ሰረገላ አቀረቡ፥ ሁሉም እያንዳንዱ አንድ በሬ በማደሪያው ፊት አቀረቡ። 4.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 5.ለመገናኛው ድንኳን ማገልገል ይሆን ዘንድ ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ስጣቸው። 6.ሙሴም ሰረገሎችንና በሬዎችን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። 7.ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው። 8.ከካህኑም ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ላሉት ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው። 9.ለቀዓት ልጆች ግን መቅደሱን ማገልገል የእነርሱ ነውና፥ በትከሻቸውም ይሸከሙት ነበርና ምንም አልሰጣቸውም። 10.መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቍርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ። 11.እግዚአብሔርም ሙሴን። አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ መባቸውን እያንዳንዱ በቀን በቀኑ ያቅርቡ አለው። 12.በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበ ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 13.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 14.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 15.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 16.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 17.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ። 18.በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ። 19.ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ድስት፤ 20.ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 21.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 22.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 23.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሶገር ልጅ የናትናኤ መባ ይህ ነበረ። 24.በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤ 25.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 26.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 27.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 28.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 29.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ። 30.በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤ 31.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 32.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 33.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 34.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 35.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሰዲዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ። 36.በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤ 37.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 38.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 39.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 40.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 41.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሱሪሰዳይ ልጅ የሰለሚኤል መባ ይህ ነበረ። 42.በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤ 43.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ማዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 44.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 45.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 46.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 47.ለደኅነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ። 48.በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤ 49.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 50.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 51.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 52.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 53.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዓሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ። 54.በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤ 55.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 56.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 57.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 58.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 59.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፍዳሱር ልጅ የገማልኤል መባ ነበረ። 60.በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤ 61.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 62.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 63.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 64.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 65.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ። 66.በአሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤ 67.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 68.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 69.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 70.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 71.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዳይ ልጅ የአኪዔዘር መባ ይህ ነበረ። 72.በአሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤ 73.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 74.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 75.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 76.ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 77.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ። 78.በአሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ፤ 79.መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 80.ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ አሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 81.ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ 82.አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 83.ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት በሬዎች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ። 84.መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች ለመቀደሻው ያቀረቡት ቍርባን ይህ ነበረ፤ አሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ አሥራ ሁለት የብር ድስቶች፥ አሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፤ 85.እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ድስት ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 86.ዕጣንም የተሞሉ አሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎች፥ እያንዳንዱ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን አሥር አሥር ሰቅል ነበረ፤ የጭልፋዎቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሀያ ሰቅል ነበረ። 87.የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ከእህሉ ቍርባን ጋር አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ አሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ አሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ነበሩ፤ የኃጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች አሥራ ሁለት ነበሩ። 88.የደኅንነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ ሀያ አራት በሬዎች፥ ስድሳም አውራ በጎች፥ ስድሳም አውራ ፍየሎች፥ ስድሳም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቀደሻው የቀረበ ቍርባን ይህ ነበረ። 89.ሙሴም ወደ መገናኛው ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በምስክሩ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛ በላይ ከኪሩቤልም መካከል ድምፁ ሲናገረው ይሰማ ነበር፤ እርሱም ይናገረው ነበር።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 13

1.ወንድማማች መዋደድ ይኑር። 2.የ እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። 3.ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ። 4.መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። 5.አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ። አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ 6.ስለዚህ በድፍረት። ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን። 7.የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። 8.ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው። 9.ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ፤ ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩባት አልተጠቀሙምና። 10.መሠዊያ አለን፥ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም። 11.ሊቀ ካህናት ስለ ኃጢአት ወደ ቅድስት የእንስሶችን ደም ያቀርባልና፤ ሥጋቸው ግን ከሰፈሩ ውጭ ይቃጠላል። 12.ስለዚህ ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ። 13.እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ፤ 14.በዚህ የምትኖር ከተማ የለችንምና፥ ነገር ግን ትመጣ ዘንድ ያላትን እንፈልጋለን። 15.እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት። 16.ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና። 17.ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ። 18.ጸልዩልን፤ በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፥ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና። 19.ይልቁንም ፈጥኜ እንድመለስላችሁ ይህን ታደርጉ ዘንድ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። 20.በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥ 21.በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 22.ወንድሞች ሆይ፥ የምክርን ቃል እንድትታገሡ እመክራችኋለሁ፥ በጥቂት ቃል ጽፌላችኋለሁና። 23.ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ እወቁ፥ ቶሎ ብሎም ቢመጣ ከእርሱ ጋር አያችኋለሁ። 24.ለዋኖቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣልያ የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 25.ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
♫
Listen to the reading 3 chapter tracks
ኦሪት ዘኍልቍ Chapter 6
ኦሪት ዘኍልቍ Chapter 7
ወደ ዕብራውያን Chapter 13
Swipe to browse chapters
Listen 3