Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 9 · ቀን 45 (አርብ) 📅 Hidar 4, 2019

ኦሪት ዘኍልቍ 6, 7 · ወደ ዕብራውያን 13

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘኍልቍ

ምዕራፍ 6

የናዝራዊነት ሥርዐት

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ ‘ወንድም ሆነ ሴት ናዝራዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመለየት ስእለት ቢሳል፣ 3.ከወይን ጠጅና ከሌላም ከሚያሰክር መጠጥ ይታቀብ፤ የወይንም ሆነ የሚያሰክር የሌላ መጠጥ ሖምጣጤ አይጠጣ፤ እንዲሁም የወይን ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን ፍሬም ሆነ ዘቢብ አይብላ። 4.በናዝራዊነቱ ወቅት ከወይን ተክል የሚገኘውን ማንኛውም ነገር፣ የወይኑን ዘር፣ ግልፋፊውንም እንኳ ቢሆን አይብላ። 5.“ ‘ስእለት ተስሎ ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ምላጭ ራሱን አይንካው፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ የተቀደሰ ይሁን፤ የራስ ጠጕሩንም ያሳድግ። 6.ራሱን ለእግዚአብሔር በለየበት ጊዜ ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ። 7.ራሱን ለእግዚአብሔር የለየበት ምልክት በራሱ ላይ ስላለ አባቱም ይሁን እናቱ፣ ወንድሙም ይሁን እኅቱ ቢሞቱ ለእነርሱ ሲል እንኳ ራሱን አያርክስ። 8.ራሱን በለየበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 9.“ ‘ድንገት ሰው አጠገቡ ሞቶ ለእግዚአብሔር የተለየበትን ጠጕሩን ቢያረክስበት፣ በሚነጻበት ዕለት ማለት በሰባተኛው ቀን ጠጕሩን ይላጭ። 10.በስምንተኛው ቀን ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ይዞ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ዘንድ ያምጣ። 11.ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት ሌላውን ማስተስረያ እንዲሆንለት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርበው፤ በሬሳ አጠገብ በመገኘቱ ኀጢአት ሠርቷልና። በዚያ ዕለት ጠጕሩን ይቀድስ። 12.ራሱን የተለየ ያደረገበትን ጊዜ ለእግዚአብሔር መቀደስ አለበት፤ እንዲሁም የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም፤ በተለየበት ጊዜ ረክሷልና። 13.“ ‘እንግዲህ ናዝራዊ የመለየቱ ጊዜ ሲያበቃ ሥርዐቱ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዲመጣ ይደረጋል። 14.እዚያም መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ይኸውም፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት እንዲሁም እንከን የሌለበት አውራ በግ ለኅብረት መሥዋዕት ሲሆን፣ 15.ከእነዚህም ጋራ የሚቀርበውን የእህልና የመጠጥ ቍርባን ቂጣ ማለት ከላመ ዱቄት በዘይት የተለወሱ ዕንጐቻዎች እንዲሁም በሥሡ የተጋገረና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ያምጣ። 16.“ ‘ካህኑ እነዚህን የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል። 17.በመሶብ ያለውን ቂጣ፣ እንዲሁም አውራ በጉን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉና ከመጠጡ ቍርባን ጋራ ካህኑ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 18.“ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጕሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነድደው እሳት ውስጥ ይጨምረው። 19.“ ‘ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጕር ከተላጨ በኋላ፣ ካህኑ የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች እንዲሁም ከመሶቡ ላይ እርሾ የሌለበትን አንድ ወፍራምና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ ናዝራዊው ያስይዘው 20.ከዚያም ካህኑ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም የተቀደሱ ናቸው። ከተወዘወዘው ፍርምባና ከቀረበው ወርች ጋራ የተቀደሱ የካህኑ ድርሻ ይሆናሉ። ከዚህ በኋላ ናዝራዊው የወይን ጠጅ መጠጣት ይችላል። 21.“ ‘ስእለቱን ለመፈጸም ለእግዚአብሔር ለሚሳል ናዝራዊ ሕጉ ይኸው ነው፤ ሊቀርብ ከሚችለው በላይ ለእግዚአብሔር ለመስጠት ቃል ለሚገባው ነገር እንደ ናዝራዊነቱ በተሳለው መሠረት መሆን አለበት። በናዝራዊነት ሕግ መሠረት የተሳለውን ስእለት መፈጸም ይገባዋል።’ ”

የካህናት ቃለ ቡራኬ

22.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ 23.“አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘እስራኤላውያንን በምትባርኩበት ጊዜ እንዲህ በሏቸው፤ 24.“ ‘ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤
ይጠብቅህም፤
25.እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፤
ይራራልህም፤
26.እግዚአብሔር ፊቱን ይመልስልህ፤
ሰላሙንም ይስጥህ።” ’
27.“በዚህ ሁኔታ ስሜን በእስራኤላውያን ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።”

ምዕራፍ 7

ማደሪያው ድንኳን ሲመረቅ የቀረቡ ስጦታዎች

1.ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን ተክሎ ካበቃ በኋላ ማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም፤ እንደዚሁም መሠዊያውንና ዕቃዎቹን በሙሉ ቀባቸው፤ ቀደሳቸውም። 2.ከዚያም የእስራኤል አለቆች ሆነው ከተቈጠሩት ነገዶች ኀላፊዎች የነበሩት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ስጦታቸውን አቀረቡ። 3.ስድስት የተሸፈኑ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት በሬዎች ይኸውም ከእያንዳንዱ አለቃ አንዳንድ በሬ እንዲሁም ከየሁለቱ አለቆች አንድ ሠረገላ ስጦታ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ፊት አመጡ፤ እነዚህንም በማደሪያው ድንኳን ፊት አቀረቧቸው። 4.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 5.“በመገናኛውም ድንኳን ለአገልግሎት እንዲውሉ እነዚህን ከእነርሱ ተቀበል፤ ለእያንዳንዳቸውም ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን ለሌዋውያኑ ስጣቸው።” 6.ስለዚህ ሙሴ ሠረገሎቹንና በሬዎቹን ወስዶ ለሌዋውያኑ ሰጣቸው፤ 7.ለጌርሶናውያን ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን ሁለት ሠረገሎችና አራት በሬዎች ሰጠ። 8.ለሜራሪያውያንም ለአገልግሎታቸው በሚያስፈልጋቸው መጠን አራት ሠረገሎችና ስምንት በሬዎች ሰጠ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ኀላፊነት የሚመሩ ነበሩ። 9.በኀላፊነት የተሰጧቸውን ንዋያተ ቅድሳት በትከሻቸው መሸከም ስለ ነበረባቸው፣ ሙሴ ለቀዓታውያን ምንም አልሰጣቸውም። 10.መሠዊያው በተቀባበት ቀን አለቆች የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ ስጦታዎችን አመጡ፤ በመሠዊያውም ፊት አቀረቡ። 11.እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ እያንዳንዱ አለቃ ስጦታውን በቀን በቀኑ ያቅርብ” አለው። 12.በመጀመሪያው ቀን ስጦታውን ያቀረበው ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበር፤ 13.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
14.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 15.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 16.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 17.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
18.በሁለተኛው ቀን የይሳኮር አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ስጦታውን አመጣ፤ 19.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
20.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 21.ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 22.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 23.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የሶገር ልጅ ናትናኤል ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
24.በሦስተኛው ቀን የዛብሎን ሕዝብ አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ስጦታውን አመጣ፤ 25.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
26.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 27.ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 28.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 29.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
30.በአራተኛው ቀን የሮቤል ሕዝብ አለቃ የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር ስጦታውን አመጣ፤ 31.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
32.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 33.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 34.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 35.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
36.በዐምስተኛው ቀን የስምዖን ሕዝብ አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ስጦታውን አመጣ፤ 37.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
38.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 39.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 40.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 41.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
42.በስድስተኛው ቀን የጋድ ሕዝብ አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ስጦታውን አመጣ፤ 43.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
44.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 45.ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 46.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 47.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
48.በሰባተኛው ቀን የኤፍሬም ሕዝብ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ስጦታውን አመጣ፤ 49.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
50.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 51.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 52.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 53.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
54.በስምንተኛው ቀን የምናሴ ሕዝብ አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ስጦታውን አመጣ፤ 55.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
56.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 57.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 58.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 59.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
60.በዘጠነኛው ቀን የብንያም ሕዝብ አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ስጦታውን አመጣ፤ 61.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
62.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 63.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 64.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 65.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
66.በዐሥረኛው ቀን የዳን ሕዝብ አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ስጦታውን አመጣ፤ 67.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
68.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 69.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው የበግ ጠቦት፣ 70.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 71.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
72.በዐሥራ አንደኛው ቀን የአሴር ሕዝብ አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ስጦታ አመጣ፤ 73.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
74.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 75.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣ 76.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 77.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ በግ፣ ዐምስት ተባዕት ፍየል እንዲሁም አንድ ዓመት የሆናቸው ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
78.በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የንፍታሌም ሕዝብ አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ስጦታውን አመጣ፤ 79.ስጦታውም፣
እያንዳንዱ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት የተሞላ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሚመዝን የብር ሳሕንና ሰባ ሰቅል የሚመዝን ከብር የተሠራ ጐድጓዳ ሳሕን፣
80.ዐሥር ሰቅል የሚመዝን በዕጣን የተሞላ የወርቅ ጭልፋ፣ 81.ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግ፣ አንድ ዓመት የሆነው ተባዕት የበግ ጠቦት፣ 82.ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ተባዕት የፍየል ጠቦት፣ 83.እንዲሁም ለኅብረት መሥዋዕት የሚቀርብ ሁለት በሬ፣ ዐምስት አውራ ፍየሎች፣ ዐምስት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ።
እንግዲህ የዔናን ልጅ አኪሬ ያቀረበው ስጦታ ይህ ነበር።
84.መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል አለቆች የመሠዊያውን መቀደስ ምክንያት በማድረግ ያቀረቧቸው ስጦታዎች እነዚህ ናቸው፤
ዐሥራ ሁለት የብር ሳሕኖች፣ ዐሥራ ሁለት ከብር የተሠሩ ጐድጓዳ ሳሕኖችና ዐሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፣
85.እያንዳንዱ የብር ሳሕን መቶ ሠላሳ ሰቅል፣ እያንዳንዱም ጐድጓዳ ሳሕን ሰባ ሰቅል፣ በአጠቃላይም የብር ሳሕኖቹ ክብደት በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺሕ አራት መቶ ሰቅል ይመዝን ነበር። 86.ዕጣን የሞላባቸው ዐሥራ ሁለቱ የወርቅ ጭልፋዎችም እያንዳንዳቸው በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ዐሥር ሰቅል መዘኑ፤ በአጠቃላይ የወርቅ ጭልፋዎቹ ክብደት አንድ መቶ ሃያ ሰቅል ነበር። 87.ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረቡት እንስሳት የእህል ቍርባናቸውን ጨምሮ ድምራቸው፦ ዐሥራ ሁለት ወይፈን፣ ዐሥራ ሁለት አውራ በግ፣ ዐሥራ ሁለት አንድ ዓመት የሆናቸው ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሆነ፤ እንዲሁም ለኀጢአት መሥዋዕት የቀረቡ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎች ነበሩ። 88.ለኅብረት መሥዋዕት የቀረቡት እንስሳት ድምር ሃያ አራት በሬ፣ ስድሳ አውራ በግ፣ ስድሳ ተባዕት ፍየልና ስድሳ አንድ ዓመት የሆናቸው ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበር።
እንግዲህ መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመሠዊያው መቀደስ የቀረቡ ስጦታዎች እነዚህ ናቸው።
89.ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋራ ለመነጋገር ወደ መገናኛው ድንኳን በገባ ጊዜ ከምስክሩ ታቦት መክደኛ በላይ በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ድምፅ ሲናገረው ሰማ፤ አነጋገረውም።
ዕብራውያን
የመጨረሻ ምክር
1 እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ።
2 እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና።
3 በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋራ እንደ ታሰራችሁ ሆናችሁ አስቧቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ አስቧቸው።
4 ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።
5 ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣
“ከቶ አልተውህም፤
በፍጹም አልጥልህም” ብሏል።
6 ስለዚህ በሙሉ ልብ፣
“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤
ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
7 የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን አስቡ፤ የኑሯቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሏቸው።
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።
9 በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ እንጂ የምግብ ሥርዐት በመጠበቅ አይደለም፤ ይህን ሥርዐት የሚጠብቁት እንኳ በዚህ አልተጠቀሙም።
10 በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን።
11 ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል።
12 እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ።
13 ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ።
14 ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን።
15 ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ።
16 ደግሞም መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋራ መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሠኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና።
17 ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጕዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው፤ አለዚያ አይበጃችሁም።
18 ለእኛ ደግሞ ጸልዩልን። በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ርግጠኞች ነን።

ቡራኬና መሰነባበቻ

19 በተለይም ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩልኝ ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ።

20 በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣

21 ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሠኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን። አሜን።

22 ወንድሞች ሆይ፤ የጻፍሁላችሁ መልእክት ዐጭር እንደ መሆኑ፣ የምክር ቃሌን በትዕግሥት እንድትቀበሉ ዐደራ እላችኋለሁ።

23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደ ተፈታ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ፤ ቶሎ ከመጣ፣ ከርሱ ጋራ ላያችሁ እመጣለሁ።

24 ለመሪዎቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

ከኢጣሊያ የሆኑትም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

25 ጸጋ ከሁላችሁ ጋራ ይሁን።