Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 9 · ቀን 44 (ሐሙስ) 📅 Hidar 3, 2019

ኦሪት ዘኍልቍ 3, 4, 5 · ወደ ዕብራውያን 12

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘኍልቍ

ምዕራፍ 3

1.እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር፤ 2.የአሮን ልጆች የበኵሩ ስም ናዳብ፣ የሌሎቹም አብዩድ አልዓዛርና ኢታምር ይባላል። 3.እርሱ ለክህነት አገልግሎት የለያቸው፣ ካህናት ለመሆን የተቀቡት የአሮን ወንድ ልጆች ስም ይህ ነው፤ 4.ናዳብና አብዩድ ግን በሲና ምድረ በዳ ባልተፈቀደ እሳት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ባቀረቡ ጊዜ እዚያው እፊቱ ወድቀው ሞቱ። ወንዶች ልጆች ስላልነበሯቸውም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን በክህነት ያገለግሉ ነበር። 5.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6.“የሌዊን ነገድ አምጥተህ ካህኑን አሮንን በአገልግሎቱ እንዲረዱት ከፊቱ አቁማቸው፤ 7.በመገናኛው ድንኳን የማደሪያውን አገልግሎት በመፈጸም ለርሱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ የሚያስፈልጉትን ተግባሮች ያከናውኑ፤ 8.የማደሪያውን ሥራ በመሥራትና የእስራኤላውያንን ግዴታ በመወጣት የመገናኛውን ድንኳን ሁሉ ይጠብቁ። 9.ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፤ እነርሱም ከእስራኤላውያን ተለይተው ለርሱ ፈጽመው የተሰጡ ናቸው። 10.አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ እነርሱም ክህነታቸውን ይጠብቁ፤ ሌላ ሰው ማደሪያውን ቢቀርብ ግን ይገደል።” 11.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12.“እነሆ፤ በኵር ሆኖ በሚወለደው ሁሉ ምትክ ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ወስጃለሁ፤ ስለዚህ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፤ 13.በኵር የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና። በግብጽ ምድር በኵር የሆነውን ሁሉ በመታሁ ዕለት ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ማንኛውንም የእስራኤልን በኵር ለራሴ ለይቻለሁ፤ የእኔ ይሁን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 14.እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ምድረ በዳ፣ 15.“ሌዋውያንን በየቤታቸውና በየጐሣቸው ቍጠር፤ የምትቈጥረውም አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ነው” አለው። 16.ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል በታዘዘው መሠረት እነዚህን ቈጠራቸው። 17.የሌዊ ልጆች ስም
ጌርሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ነው።
18.የጌርሶን ልጆች ጐሣ ስም
ሎቤኒና ሰሜኢ ነው።
19.የቀዓት ጐሣዎች፤
እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮን፣ ዑዝኤል።
20.የሜራሪ ጐሣዎች፤
ሞሖሊና ሙሲ።
እንግዲህ የሌዋውያን ጐሣዎች በየቤተ ሰባቸው ሲቈጠሩ እነዚህ ናቸው።
21.የሊብናና የሰሜኢ ጐሣዎች ከጌርሶን ወገን ናቸው፤ እነዚህ የጌርሶን ጐሣዎች ነበሩ። 22.አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ሰባት ሺሕ ዐምስት መቶ ነበር። 23.የጌርሶን ጐሣዎች በምዕራብ በኩል ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ይሰፍራሉ። 24.የጌርሶን ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። 25.የጌርሶናውያን ኀላፊነት በመገናኛው ድንኳን ማደሪያውንና ድንኳኑን፣ መደረቢያዎቹን እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያለውን መጋረጃ፣ 26.የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ ማደሪያ ድንኳኑንና መሠዊያውን የሚጋርደውን የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፣ ገመዶቹንና ከነዚሁ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ መጠበቅ ይሆናል። 27.የእንበረማውያን፣ የይስዓራውያን፣ የኬብሮናውያንና የዑዝኤላውያን ጐሣዎች ከቀዓት ወገን ናቸው፤ እነዚህ የቀዓት ጐሣዎች ነበሩ። 28.አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች በሙሉ ብዛታቸው ስምንት ሺሕ ስድስት መቶ ሲሆን፣
ቀዓታውያንም መቅደሱን የመጠበቅ ኀላፊነት ነበራቸው።
29.የቀዓት ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። 30.የቀዓት ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊጻፋን ይሆናል። 31.እነርሱም ታቦቱን፣ ጠረጴዛውን፣ መቅረዙን፣ መሠዊያዎቹን፣ ለመቅደሱ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች፣ መጋረጃዎችንና ከነዚህ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ይጠብቃሉ። 32.ዋናው የሌዋውያን አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው፤ እርሱም መቅደሱን ለመጠበቅ ኀላፊ በሆኑት ላይ ተሹሞ ነበር። 33.የሞሖላውያንና የሙሳያውያን ጐሣዎች ከሜራሪ ወገን ናቸው፤ እነዚህም የሜራሪ ጐሣዎች ነበሩ። 34.አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተቈጠሩት ወንዶች ሁሉ ብዛታቸው ስድስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበር። 35.የሜራሪም ጐሣዎች ቤተ ሰቦች አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ይሆናል፤
የሜራሪም ጐሣዎች ከማደሪያው ድንኳን በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።
36.ሜራሪያውያንም የማደሪያውን ድንኳን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን እግሮች፣ የማደሪያ ዕቃዎችን ሁሉና ከነዚሁ ጋራ ተያይዞ አገልግሎት የሚሰጠውን ሁሉ ለመጠበቅ ተሹመው ነበር። 37.እንዲሁም የአደባባዩን ዙሪያ ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ከነካስማቸውና ከነገመዶቻቸው ይጠብቃሉ። 38.ሙሴ፣ አሮንና ልጆቹ ከማደሪያው ድንኳን በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይሰፍራሉ።
እነርሱም እስራኤላውያንን ወክለው ማደሪያ ድንኳኑን ለመጠበቅ ኀላፊዎች ይሆናሉ።
ወደ ማደሪያው ድንኳን የሚቀርብ ማንኛውም ሌላ ሰው ግን ይገደል።
39.አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው፣ ሙሴና አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በየጐሣቸው የቈጠሯቸው የሌዋውያን ወንዶች ልጆች ጠቅላላ ብዛት ሃያ ሁለት ሺሕ ነበር። 40.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ። 41.በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 42.ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤ 43.አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር። 44.ደግሞም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 45.“በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 46.ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣ 47.ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ልክ ዐምስት ዐምስት ሰቅል ተቀበል፤ 48.የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” 49.ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤ 50.ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ስድሳ ዐምስት ሰቅል ሰበሰበ። 51.ሙሴም በእግዚአብሔር ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።

ምዕራፍ 4

ቀዓታውያን

1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2.“ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሩ። 3.እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠሩ። 4.“በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅድሳቱን መጠበቅ ነው። 5.ሰፈሩ ሲነሣ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ 6.ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ። 7.“በገጸ ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁልጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ። 8.በእነዚህም ላይ ቀይ ጨርቅ ይዘርጉ፤ የአቆስጣውን ቍርበት ደርበውም መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። 9.“ደግሞም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው ማብሪያ መቅረዙንና መብራቶቹን፣ መኰስተሪያዎቹንና የኵስታሪ መቀበያዎቹን፣ እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን የዘይት ዕቃዎች ይሸፍኑበት። 10.ከዚያም ይህንና ከዚሁ ጋራ የተያያዙትን ዕቃዎች ሁሉ በአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት። 11.“በወርቅ መሠዊያ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ዘርግተው በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። 12.“እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት። 13.“ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤ 14.ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። 15.“አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅድሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው። 16.“የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።” 17.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 18.“የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤ 19.ወደ ንዋየ ቅድሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት። 20.ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”

ጌድሶናውያን

21.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 22.“ጌርሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቍጠራቸው፤ 23.ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቍጠር። 24.“የጌርሶናውያን ወገኖች የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤ 25.እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤ 26.እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ። 27.የጌርሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ። 28.እንግዲህ የጌርሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል።

ሜራሪያውያን

29.“ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቍጠራቸው፤ 30.እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠር። 31.በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤ 32.እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋራ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት። 33.እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።”

የሌዋውያን ጐሣዎች ቈጠራ

34.ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው። 35.ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣ 36.በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ዐምሳ ነበሩ። 37.ይህ ከቀዓት ጐሣዎች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው። ሙሴና አሮን፣ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ቈጠሯቸው። 38.ጌርሶናውያን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር። 39.በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ 40.በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 41.ይህ ከጌርሶን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው። 42.ሜራሪያውያንም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር። 43.በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ 44.በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ። 45.ይህ የሜራሪ ጐሣዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው። 46.ስለዚህ ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች ሌዋውያኑን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው፤ 47.ከሠላሳ እስከ ዐምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ለመስጠትና ለመሸከም የመጡት፣ 48.ቍጥራቸው ስምንት ሺሕ ዐምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። 49.እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ በየአገልግሎቱና በየሸክም ሥራው ተደለደለ።
ስለዚህም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ቈጠራቸው።

ምዕራፍ 5

የሰፈሩ መንጻት

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበትን ወይም ማንኛውም ዐይነት ፈሳሽ ከሰውነቱ የሚወጣውን ወይም ሬሳ በመንካቱ በሥርዐቱ መሠረት የረከሰውን ሰው ሁሉ ከሰፈር እንዲያስወጡ እስራኤላውያንን እዘዝ፤ 3.ወንድም ሆነ ሴት አስወጡ፤ እኔ በመካከላቸው የምኖርበትን ሰፈራቸውን እንዳያረክሱ ከሰፈር አስወጧቸው።” 4.እስራኤላውያን ይህንኑ አደረጉ፤ ሰዎቹንም ከሰፈር አስወጧቸው፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘውም መሠረት ፈጸሙ።

የካሳ አከፋፈል

5.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6.“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ወንድም ሆነ ሴት በማናቸውም ረገድ ሌላውን ቢበድልና ከዚህም የተነሣ ለእግዚአብሔር ባይታመን በደለኛ ነው 7.በሠራው ኀጢአት ይናዘዝ፤ ስለ በደሉም ሙሉ ካሳ ይክፈል፤ የተመደበበትም ካሳ ላይ አንድ ዐምስተኛ በመጨመር በደል ላደረሰበት ሰው ይስጥ፤ 8.ነገር ግን ይህ ሰው ካሳውን የሚቀበልለት ዘመድ ከሌለው ካሳው ለእግዚአብሔር ስለሚሆን ማስተስረያ እንዲሆነው ከሚያቀርበው አውራ በግ ጋራ ለካህኑ ይስጥ። 9.እስራኤላውያን የሚያመጧቸው የተቀደሱ ስጦታዎች ሁሉ ለተቀባዩ ካህን ይሆናሉ፤ 10.የእያንዳንዱ ሰው የተቀደሰ ስጦታ ለካህኑ ይሆናል፤ ለካህኑ የሚሰጠውም ሁሉ የራሱ ይሆናል።’ ”

በአመንዝራነት ስለሚጠረጠሩ ሚስቶች

11.ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12.“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘አንዲት ባለትዳር ሴት ወደ ሌላ ወንድ በማዘንበል ለባሏ ባትታመን፣ 13.ከሌላ ሰው ጋራ ብትተኛ፣ ይህም እጅ ከፍንጅ ባለመያዟ ምክንያት ይህ ከባሏ ቢደበቅ፣ የሚመሰክርባት ሰው ባይኖርና መርከሷም ባይገለጥ፣ 14.ባሏ የቅናት መንፈስ ዐድሮበት ቢጠረጥርና በርግጥም ጐድፋ ብትገኝ ወይም ባሏ የቅናት መንፈስ ዐድሮበት ቢጠረጥርና እርሷ ግን ጐድፋ ባትገኝ፣ 15.ወደ ካህኑ ይውሰዳት፤ ስለ እርሷም አንድ ኪሎ ገብስ ዱቄት ለቍርባን ይውሰድ፤ በላዩ ላይ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ ይህ ስለ ቅናት የቀረበ የእህል ቍርባን በደልን የሚያሳስብ የመታሰቢያ ቍርባን ነውና። 16.“ ‘ካህኑ ሴትዮዋን ያመጣትና በእግዚአብሔር ፊት እንድትቆም ያደርጋታል፤ 17.ከዚያም ካህኑ የተቀደሰ ውሃ በሸክላ ዕቃ ቀድቶ በማደሪያው ድንኳን ካለው ወለል ጥቂት ዐፈር ቈንጥሮ በውሃው ውስጥ ይጨምራል። 18.ካህኑ ሴትዮዋን በእግዚአብሔር ፊት እንድትቆም ካደረገ በኋላ የጠጕሯን መሸፈኛ ይገልጣል፤ ስለ ቅናት የቀረበውን የመታሰቢያ ቍርባን በእጇ ያስይዛታል፤ ከዚያም ካህኑ ርግማን የሚያመጣውን መራራ ውሃ በእጁ ይይዛል። 19.ካህኑም ሴትዮዋን ያስምላታል፤ እንዲህም ይላታል፤ “ሌላ ወንድ ዐብሮሽ ካልተኛ፣ በትዳር ላይ ሆነሽ ወደ ርኩሰት ካላዘነበልሽ ይህ ርግማን የሚያመጣ መራራ ውሃ ጕዳት አያድርስብሽ፤ 20.ነገር ግን በትዳር ላይ እያለሽ ወደ ርኩሰት በማዘንበል ከባልሽ ሌላ ከወንድ ጋራ በመተኛት ከጐደፍሽ”፣ 21.እዚህ ላይ ካህኑ እንዲህ በማለት ሴትዮዋን በርግማን መሐላ ያስምላታል፤ “እግዚአብሔር ጭንሽን እያሰለለና ሆድሽን እያሳበጠ በሕዝብሽ መካከል ርግማንና መሐላ ያድርግብሽ፤ 22.ይህን ርግማን የሚያመጣ ውሃ በጠጣሽ ጊዜም ሆድሽን ያሳብጠው፤ ጭንሽን ያስልለው።”
“ ‘ሴትዮዋም፣ “አሜን፤ አሜን” ትበል።
23.“ ‘ካህኑ እነዚህን መርገሞች በሰሌዳ ላይ ይጻፍ፤ በመራራውም ውሃ ይደምስሳቸው። 24.ርግማን የሚያመጣውንም ውሃ ሴትዮዋ እንድትጠጣ ያድርግ፤ ውሃውም ወደ ሰውነቷ ገብቶ የመረረ ሥቃይ ያስከትልባታል። 25.ካህኑ ለቅናት የቀረበውን የእህል ቍርባን ይቀበላት፤ በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዞ ወደ መሠዊያው ያቅርበው። 26.ካህኑ የመታሰቢያ ቍርባን እንዲሆን ዕፍኝ የእህል ቍርባን ከዚያ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ከዚያም በኋላ ሴቲቱ ውሃውን እንድትጠጣ ያድርግ። 27.ራሷን በማጕደፍ ለባሏ ባትታመን፣ ርግማን የሚያመጣውን ውሃ እንድትጠጣ ሲደረግ ውሃው ወደ ሰውነቷ ገብቶ ክፉ ሥቃይ ያመጣባታል፤ ሆዷ ያብጣል፤ ጭኗ ይሰልላል፤ በሕዝቦቿም ዘንድ የተረገመች ትሆናለች። 28.ዳሩ ግን ሴትዮዋ ካልጐደፈችና ነውር ከሌለባት ከበደሉ ነጻ ትሆናለች፤ ልጆችም ትወልዳለች። 29.“ ‘እንግዲህ የቅናት ሕግ ይህ ነው፤ አንዲት ሴት በትዳር ላይ እያለች ወደ ሌላ ሄዳ ከረከሰች፣ 30.ወይም አንድ ሰው ሚስቱን ከመጠርጠሩ የተነሣ የቅናት መንፈስ ሲያድርበት በእግዚአብሔር ፊት ያቁማት፤ ካህኑም ሕጉ በሙሉ በሴቲቱ ላይ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያድርግ። 31.ባልየውም ከበደል ንጹሕ ይሆናል፤ ሴትዮዋ ግን በበደሏ ምክንያት የሚመጣውን ፍዳ ትቀበላለች።’ ”

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 12

1.እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ። 2.የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል። 3.እንግዲህ ዝላችሁ ተስፋ እንዳትቈርጡ፣ ከኀጢአተኞች የደረሰበትን እንዲህ ያለውን ተቃውሞ የታገሠውን እርሱን አስቡ።

እግዚአብሔር ልጆቹን ይቀጣል

4.ከኀጢአት ጋራ ስትታገሉ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም። 5.ልጆች እንደ መሆናችሁ እንዲህ በማለት የተናገራችሁን ማበረታቻ ቃልም ረስታችኋል፦
“ልጄ ሆይ፤ የጌታን ተግሣጽ አታቃልል፤
በሚቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቍረጥ፤
6.ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤
እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።”
7.እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዟችኋልና የተግሣጽን ምክር ታገሡ፤ ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? 8.ልጆች ሁሉ በሚቀጡበት ቅጣት ተካፋይ ካልሆናችሁ፣ ዲቃሎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም። 9.ከዚህም በላይ፣ እኛ ሁላችን የሚቀጡን ምድራዊ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር። ታዲያ ለመናፍስት አባት እንዴት አብልጠን በመገዛት በሕይወት አንኖርም! 10.አባቶቻችን መልካም መስሎ እንደ ታያቸው ለጥቂት ጊዜ ይቀጡን ነበር፤ እግዚአብሔር ግን የቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን ለእኛ ጥቅም ሲል ይቀጣናል። 11.ቅጣት ሁሉ በወቅቱ የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፤ በኋላ ግን ለለመዱት ሰዎች የጽድቅና የሰላም ፍሬ ያስገኝላቸዋል። 12.ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ። 13.ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።”

እግዚአብሔርን ስላለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

14.ከሰው ሁሉ ጋራ በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። 15.ከእናንተ ማንም የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይጐድልበት፣ ደግሞም መራራ ሥር በቅሎ ችግር እንዳያስከትልና ብዙዎችን እንዳይበክል ተጠንቀቁ። 16.ለአንድ ጊዜ መብል ሲል ብኵርናውን እንደ ሸጠው እንደ ዔሳው፣ ማንም ሴሰኛ ወይም እግዚአብሔርን የማያከብር ሆኖ እንዳይገኝ ተጠንቀቁ። 17.በኋላም ይህንኑ በረከት ሊወርስ በፈለገ ጊዜ እንደ ተከለከለ ታውቃላችሁ፤ በረከቱን በእንባ ተግቶ ቢፈልግም ለንስሓ ስፍራ ሊያገኝ አልቻለም።

የፍርሀት ተራራና የደስታ ተራራ

18.ሊዳሰስ ወደሚችለውና በእሳት ወደሚቃጠለው ተራራ፣ ወደ ጨለማው፣ ወደ ጭጋጉና ወደ ዐውሎ ነፋሱ አልደረሳችሁም፤ 19.ወደ መለከት ድምፅ ወይም ቃልን ወደሚያሰማ ድምፅ አልመጣችሁም፤ የሰሙትም ሌላ ቃል ተጨምሮ እንዳይናገራቸው ለመኑ። 20.ምክንያቱም “እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ፣ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት” የሚለውን ትእዛዝ መሸከም አልቻሉም። 21.በዚያ ይታይ የነበረውም ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነበርና፣ ሙሴ “በፍርሀት ተንቀጠቀጥሁ” አለ። 22.እናንተ ግን ወደ ጽዮን ተራራ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ መጥታችኋል፤ በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ 23.ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈው ወደ በኵራት ማኅበር ቀርባችኋል፤ የሁሉ ዳኛ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹምነትን ወዳገኙት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ 24.የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ፣ እንዲሁም ከአቤል ደም የተሻለ ቃል ወደሚናገረው ወደ ተረጨው ደም ደርሳችኋል። 25.የሚናገረውን እርሱን እንቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነቅቃቸው የነበረውን እንቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ከርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? 26.በዚያ ጊዜ ድምፁ ያናወጠው ምድርን ነበር፤ አሁን ግን፣ “አንድ ጊዜ እንደ ገና ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አናውጣለሁ” ብሎ ቃል ገብቷል። 27.አንድ ጊዜ “ደግሜ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የማይናወጡት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ፣ የሚናወጡት ይኸውም፣ የተፈጠሩት የሚወገዱ መሆናቸውን ነው። 28.ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤ 29.“አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።”