Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 9 · ቀን 43 (ረቡዕ) 📅 Hidar 2, 2019

ኦሪት ዘኍልቍ 1, 2 · መዝሙረ ዳዊት 64 · ወደ ዕብራውያን 11

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘኍልቍ

ምዕራፍ 1

የሕዝብ ቈጠራ

1.እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን በሲና ምድረ በዳ ሳሉ እግዚአብሔር ሙሴን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤ 2.“የወንዶቹን ስም አንድ በአንድ በመዘርዘር መላውን የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሯቸው። 3.በመላው እስራኤል ያሉትን ዕድሜያቸው ሃያና ከዚያም በላይ ሆኖ ለውጊያ ብቁ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንተና አሮን በየምድባቸው ቍጠሯቸው። 4.ከየነገዱ የአባቶች ቤት ተጠሪ የሆነ አንድ ሰው ከእናንተ ጋራ ይሁን። 5.“የሚረዷችሁም ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤
“ከሮቤል የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤
6.ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤ 7.ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፤ 8.ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፤ 9.ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤ 10.ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤
ከምናሴ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤
11.ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤ 12.ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤ 13.ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤ 14.ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤ 15.ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ።” 16.እነዚህ ከማኅበረ ሰቡ የተመረጡ የየነገዱ አለቆች ሲሆኑ እነርሱም የእስራኤል ጐሣዎች መሪዎች ነበሩ። 17.ሙሴና አሮን ስማቸው የተጠቀሰውን እነዚህን ሰዎች ወሰዱ፤ 18.ከዚያም በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበረ ሰቡን በሙሉ በአንድነት ሰበሰቧቸው። የተሰበሰቡትም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የትውልድ ሐረጋቸውን ተናገሩ፤ 19.እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነ ወንዶች ስማቸው አንድ በአንድ ተመዘገበ። እንዲህ አድርጎም በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው። 20.ከእስራኤል የበኵር ልጅ ከሮቤል ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኖ በሰራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
21.ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ። 22.ከስምዖን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
23.ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት ዐምሳ ዘጠኝ ሺሕ ሦስት መቶ ነበሩ። 24.ከጋድ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
25.ከጋድ ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ዐምስት ሺሕ ስድስት መቶ ዐምሳ ነበሩ። 26.ከይሁዳ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
27.ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩትም ሰባ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ነበሩ። 28.ከይሳኮር ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
29.ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ አራት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ። 30.ከዛብሎን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
31.ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሰባት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ። 32.ከዮሴፍ ልጆች፦
ከኤፍሬም ዝርያ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
33.ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ። 34.ከምናሴ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
35.ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ። 36.ከብንያም ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ፤
37.ከብንያም ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ዐምስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ። 38.ከዳን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
39.ከዳን ነገድ የተቈጠሩትም ስድሳ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ነበሩ። 40.ከአሴር ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
41.ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ። 42.ከንፍታሌም ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ።
43.ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ። 44.በሙሴና በአሮን፣ እያንዳንዳቸውም ቤተ ሰባቸውን በወከሉት በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል አለቆች የተቈጠሩት ወንዶች እነዚህ ናቸው። 45.ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ በእስራኤል ሰራዊት ውስጥ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት በየቤተ ሰባቸው ተቈጠሩ፤ 46.ጠቅላላ ቍጥራቸውም ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ነበር። 47.የሌዊ ነገድ ቤተ ሰቦች ግን ከሌሎች ጋራ ዐብረው አልተቈጠሩም፤ 48.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበርና፤ 49.“የሌዊን ነገድ አትቍጠር፤ በእስራኤላውያንም ቈጠራ ውስጥ አታስገባው፤ 50.በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በምስክሩ ማደሪያ፣ በውስጡ ባሉት በመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ከዚሁ ጋራ በተያያዙ በማናቸውም ነገሮች ላይ ኀላፊዎች ይሁኑ፤ ማደሪያውንና በውስጡ ያሉትን የመገልገያ ዕቃዎች ይሸከሙ፤ በውስጡ ያገልግሉ፤ ድንኳናቸውንም በዙሪያው ይትከሉ። 51.ማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያው በሚተከልበትም ጊዜ ሌዋውያን ያቁሙት፤ ሌላ ሰው ቢቀርብ ግን ይገደል። 52.እስራኤላውያን በየምድባቸው ድንኳናቸውን ይትከሉ፤ እያንዳንዱም ሰው በየሰፈሩና በየዐርማው ሥር ይስፈር። 53.ሌዋውያን ግን በእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ድንኳኖቻቸውን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይትከሉ፤ የምስክሩ ማደሪያ ድንኳን ኀላፊዎች ሌዋውያን ናቸው።” 54.እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ይህን ሁሉ አደረጉ።

ምዕራፍ 2

የየነገዱ አሰፋፈር

1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2.“እስራኤላውያን ከምስክሩ ድንኳን ትይዩ ዙሪያውን ጥቂት ራቅ ብለው እያንዳንዱ ሰው በየዐርማውና በየቤተ ሰቡ ምልክት ሥር ይስፈር።” 3.በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ፤
የይሁዳ ምድብ፤ በየሰራዊቱና በዐርማቸው ሥር ይስፈር፤ የይሁዳ ሕዝብ አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነው፤
4.የሰራዊቱም ብዛት ሰባ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ነው። 5.ከእነዚህ ቀጥሎ የይሳኮር ነገድ ይሰፍራል፤ የይሳኮር ሕዝብ አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ሲሆን፣ 6.የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ አራት ሺሕ አራት መቶ ነው። 7.ከዚያም የዛብሎን ነገድ ይቀጥላል፤ የዛብሎን ሕዝብ አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ሲሆን፣ 8.የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ሰባት ሺሕ አራት መቶ ነው። 9.በየሰራዊታቸው ሆነው ከአይሁድ ምድብ የተመዘገቡ አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺሕ አራት መቶ ናቸው፤ እነዚህ አስቀድመው ይወጣሉ። 10.በደቡብ በኩል፤
የሮቤል ምድብ ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ይሆናል፤ የሮቤል ሕዝብ አለቃ የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር ሲሆን፣
11.የሰራዊቱም ብዛት አርባ ስድስት ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 12.ከእነዚህ ቀጥሎ የስምዖን ነገድ ይሰፍራል፤ የስምዖን ሕዝብ አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ሲሆን፣ 13.የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ዘጠኝ ሺሕ ሦስት መቶ ነው። 14.ከዚያም የጋድ ነገድ ይቀጥላል፤ የጋድ ሕዝብ አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ሲሆን፣ 15.የሰራዊቱም ብዛት አርባ ዐምስት ሺሕ ስድስት መቶ ዐምሳ ነው። 16.በየሰራዊታቸው ሆነው ከሮቤል ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ አንድ መቶ ዐምሳ አንድ ሺሕ አራት መቶ ዐምሳ ናቸው፤ እነዚህ ቀጥለው ይመጣሉ። 17.ከዚህ በኋላ የመገናኛው ድንኳንና የሌዋውያን ምድብ በመካከል ሆነው ይጓዛሉ፤ እያንዳንዳቸውም አሰፋፈራቸውን በመከተል ቦታቸውን ጠብቀው በዐርማቸው ሥር ይጓዛሉ። 18.በምዕራብ በኩል፤
የኤፍሬም ምድብ ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ይሆናል፤ የኤፍሬም ሕዝብ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ሲሆን፣
19.የሰራዊቱም ብዛት አርባ ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 20.ከእነዚህም የምናሴ ነገድ ይቀጥላል፣ የምናሴ ሕዝብ አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ሲሆን፣ 21.የሰራዊቱም ብዛት ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ነው። 22.ከዚያም የብንያም ነገድ ይቀጥላል፣ የብንያም ሕዝብ አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ሲሆን፣ 23.የሰራዊቱም ብዛት ሠላሳ ዐምስት ሺሕ አራት መቶ ነው። 24.በየሰራዊታቸው ሆነው ከኤፍሬም ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ አንድ መቶ ስምንት ሺሕ አንድ መቶ ናቸው፤ እነዚህ ሦስተኛ ሆነው ይመጣሉ። 25.በሰሜን በኩል፤
የዳን ምድብ ሰራዊት በዐርማው ሥር ይሆናል፤ የዳን ሕዝብ አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ሲሆን፣
26.የሰራዊቱም ብዛት ስድሳ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ነው። 27.የአሴር ነገድ ከእነዚህ ቀጥሎ ይሰፍራል፤ የአሴር ሕዝብ አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ሲሆን፣ 28.የሰራዊቱም ብዛት አርባ አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 29.ከዚያም የንፍታሌም ነገድ ይቀጥላል፤ የንፍታሌም ሕዝብ አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ሲሆን፣ 30.የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ነው። 31.በየሰራዊታቸው ሆነው ከዳን ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች ሁሉ አንድ መቶ ዐምሳ ሰባት ሺሕ ስድስት መቶ ናቸው፤ እነርሱም በዐርማቸው ሥር በመጨረሻ ይመጣሉ። 32.በየቤተ ሰባቸው፣ በየምድባቸውና በየሰራዊታቸው የተመዘገቡት እስራኤላውያን ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ናቸው፤ 33.ያም ሆኖ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሌዋውያኑ ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ አልተቈጠሩም። 34.ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ በየዐርማውም ሥር የሰፈሩትና፣ እያንዳንዳቸው በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተጓዙት በዚህ ሁኔታ ነበር።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 64

1.ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤
ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት።
2.ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤
ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ።
3.እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤
መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ።
4.አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤
ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም።
5.ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤
በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤
“ማንስ ሊያየን ይችላል?” ይባባላሉ።
6.ግፍን ያውጠነጥናሉ፤
ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤
አቤት! የሰው ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው!
7.እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤
እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።
8.በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤
ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤
የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።
9.የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤
የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤
ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ።
10.ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤
እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤
ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 11

የእምነት ቋሚ ምስክሮች

1.እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም ርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው። 2.አባቶችም የተመሰከረላቸው በዚሁ ነው። 3.ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠሩ በእምነት እንረዳለን፤ ስለዚህ የሚታየው ነገር የተፈጠረው ከሚታየው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። 4.አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል። 5.ሔኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ “እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም”፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሠኘ ተመስክሮለታልና። 6.ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። 7.ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። 8.አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ ዕሺ ብሎ ሄደ። 9.በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋዪቱ ምድር በእምነት ተቀመጠ፤ የተስፋውን ቃል ዐብረውት እንደሚወርሱት እንደ ይሥሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ኖረ፤ 10.ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር። 11.አብርሃም ምንም እንኳ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሣራም ራሷ መካን ብትሆንም፣ ተስፋን የሰጠውን ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረ በእምነት የልጅ አባት ለመሆን በቃ። 12.ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። 13.እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና። 14.እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያሳያሉ። 15.ትተዉት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው። 16.አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። 17.አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይሥሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ 18.ይህም እግዚአብሔር፣ “ዘርህ በይሥሐቅ ይጠራል” ያለለት ነበር። 19.አብርሃም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ይሥሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው። 20.ይሥሐቅ ወደ ፊት የሚሆነውን ዐስቦ ያዕቆብንና ዔሳውን በእምነት ባረካቸው። 21.ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ እያንዳንዳቸውን የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው፤ በበትሩም ጫፍ ዘንበል ብሎ ሰገደ። 22.ዮሴፍ ሊሞት በተቃረበ ጊዜ፣ ስለ እስራኤል ሕዝብ ከግብጽ መውጣት በእምነት ተናገረ፤ ስለ ዐፅሙም ትእዛዝ ሰጠ። 23.ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም። 24.ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። 25.ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋራ መከራን መቀበል መረጠ። 26.ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና። 27.የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብጽን ለቅቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በሐሳቡ ጸና። 28.በኵሮች የሆኑትን የሚገድለው ቀሣፊ የእስራኤልን በኵር ልጆች እንዳይገድል ፋሲካን በእምነት አደረገ፤ ደምንም ረጨ። 29.ሕዝቡ በደረቅ መሬት እንደሚኬድ ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ግብጻውያን ግን እንደዚሁ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰጠሙ። 30.ሕዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ፣ በእምነት ወደቀ። 31.ዝሙት ዐዳሪዋ ረዓብ፣ ሰላዮቹን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋራ ያልጠፋችው በእምነት ነው። 32.እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ እንዲሁም ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ የለም። 33.እነዚህ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በቅን ፈረዱ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀበሉ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ 34.የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ፤ ባዕዳን ወታደሮችን አባረሩ። 35.ሴቶች፣ ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። 36.አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ 37.በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ 38.ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጕድጓዱ ተንከራተቱ። 39.እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም፣ ከእነርሱ ማንም የተስፋውን ቃል የተቀበለ የለም፤ 40.እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ፣ ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አልቻሉምና።