ሳምንት 9 · ቀን 42 (ማክሰኞ)
📅 Hidar 1, 2019
ኦሪት ዘሌዋውያን 26, 27 · መዝሙረ ዳዊት 112 · ወደ ዕብራውያን 10
ኦሪት ዘሌዋውያን
ምዕራፍ 26
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
1.“ ‘ትሰግዱላቸው ዘንድ ጣዖታትን አታብጁ፤ ምስል ወይም የማምለኪያ ዐምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 2.“ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3.“ ‘በሥርዐቴ ብትሄዱ፣ ትእዛዜንም በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ 4.ዝናብን በወቅቱ እሰጣችኋለሁ፤ ምድሪቱ እህሏን፣ የሜዳ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። 5.የምትወቁት እህል፣ የወይን ዘለላ እስከምትቈርጡበት ጊዜ፣ የምትቈርጡትም የወይን ዘለላ፣ እህል እስከምትዘሩበት ጊዜ ያደርሷችኋል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ላይ ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። 6.“ ‘በምድሪቱ ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፤ ትተኛላችሁ፤ ማንም አያስፈራችሁም። ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። 7.ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነርሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 8.ከእናንተ ዐምስቱ መቶውን፣ መቶውም ዐሥሩን ሺሕ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 9.“ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋራ አጸናለሁ። 10.የዓምናውን እህል እየበላችሁ ከጐተራው ሳያልቅ ለዘንድሮው እህል ደግሞ ቦታ ታስለቅቃላችሁ። 11.ማደሪያዬን በመካከላችሁ አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12.በመካከላችሁ እመላለሳለሁ፤ አምላካችሁ እሆናለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ። 13.ለግብጻውያን ባሪያዎች እንዳትሆኑ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነት ቀንበራችሁን ሰብሬ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት
14.“ ‘ነገር ግን ባትሰሙኝ፣ እነዚህን ትእዛዞች ባትጠብቁ፣ 15.ሥርዐቴን ብትንቁ፣ ሕጌን ብታቃልሉ፣ ትእዛዞቼንም ሁሉ ባለመፈጸም ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፣ 16.እኔም ይህን አደርግባችኋለሁ፤ ድንገተኛ ድንጋጤ፣ የሚቀሥፍ በሽታ፣ ዐይናችሁን የሚያጠፋና ሰውነታችሁን የሚያመነምን ትኵሳት አመጣባችኋለሁ፤ እህል የምትዘሩት በከንቱ ነው፤ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17.በጠላቶቻችሁ ድል እንድትሆኑ ፊቴን በእናንተ ላይ አከብድባችኋለሁ፤ የሚጠሏችሁ ይገዟችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁም ትሸሻላችሁ። 18.“ ‘ከዚህ ሁሉ በኋላ ባትታዘዙኝ፣ ስለ ኀጢአታችሁ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ፤ 19.የትዕቢታችሁን ኀይል እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20.ኀይላችሁ በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁ እህሏን፣ የምድሪቱ ዛፎችም ፍሬዎቻቸውን አይሰጡምና። 21.“ ‘በእኔ ላይ ማመፅ ብትቀጥሉና ባትታዘዙኝ እንደ ኀጢአታችሁ መጠን ሰባት ዕጥፍ መቅሠፍት እጨምርባችኋለሁ። 22.የዱር አራዊትን እሰድድባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤ ከብቶቻችሁን ያጠፉባችኋል፤ ቍጥራችሁ ይመነምናል፤ መንገዶቻችሁም ሰው አልባ ይሆናሉ። 23.“ ‘በዚህ ሁሉ ግን ወደ እኔ ባትመለሱ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ 24.እኔም ጠላት እሆንባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም ሰባት ዕጥፍ አስጨንቃችኋለሁ። 25.ቃል ኪዳኔን ስላፈረሳችሁ፣ በላያችሁ ሰይፍ በማምጣት እበቀላችኋለሁ፤ በከተሞቻችሁ ውስጥ በምትሰበሰቡበት ጊዜ ቸነፈር እሰድድባችኋለሁ፤ ለጠላትም እጅ ዐልፋችሁ ትሰጣላችሁ። 26.የእንጀራችሁ እህል እንዲቋረጥ በማደርግበት ጊዜ፣ ዐሥር ሴቶች በአንድ ምጣድ ላይ እንጀራ ይጋግራሉ፤ እንጀራውንም በሚዛን መዝነው እናንተም ትበላላችሁ፤ ግን አትጠግቡም። 27.“ ‘በዚህ ሁሉ ግን ባትታዘዙኝ፣ በእኔም ላይ ማመፃችሁን ብትቀጥሉ፣ 28.እኔም በቍጣዬ እመጣባችኋለሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁም እኔው ራሴ ሰባት ዕጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29.የወንዶች ልጆቻችሁን ሥጋና የሴቶች ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ። 30.የኰረብታ መስገጃዎቻችሁን እደመስሳለሁ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁን አፈርሳለሁ፤ በድኖቻችሁን በድን በሆኑት ጣዖቶቻችሁ ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31.ከተሞቻችሁን አፈራርሳለሁ፤ መቅደሶቻችሁንም ወና አደርጋለሁ፤ ጣፋጭ ሽታ ያለውን መሥዋዕታችሁንም አልቀበልም። 32.በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁ እስኪደነቁ ድረስ፣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ። 33.በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ሰይፌን መዝዤም አሳድዳችኋለሁ። ምድራችሁ ባድማ፣ ከተሞቻችሁም ፍርስራሽ ይሆናሉ። 34.ምድሪቱ ባድማ በሆነችበት ጊዜ ሁሉና እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር በምትኖሩበት ወቅት ምድሪቱ በሰንበት ዓመቷ ትደሰታለች፤ ምድሪቱም በሰንበቷ ታርፋለች፤ ትደሰታለችም። 35.ምድሪቱ እናንተ በነበራችሁባት ጊዜ በሰንበት ያላገኘችውን ዕረፍት፣ ባድማ በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ታገኛለች። 36.“ ‘ከእናንተ በሕይወት የተረፉትን፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ድንጋጤ እሰድድባቸዋለሁ፤ ነፋስ የሚያንቀሳቅሰው የቅጠል ድምፅ ያስበረግጋቸዋል፤ የሚያሳድዳቸውም ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሮጣሉ፤ ይወድቃሉም። 37.የሚያሳድዳቸው ሳይኖር ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ በጠላቶቻችሁም ፊት መቆም አትችሉም። 38.በአሕዛብ መካከል ታልቃላችሁ፤ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39.ከእናንተ የተረፉት በጠላቶቻቸው ምድር በራሳቸው ኀጢአትና በአባቶቻቸው ኀጢአት ምክንያት መንምነው ያልቃሉ። 40.“ ‘ነገር ግን ለእኔ ያልታመኑበትንና በእኔም ላይ ያመፁበትን የራሳቸውን ኀጢአትና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ 41.ይኸውም፣ እኔ ጠላት እንድሆንባቸውና ወደ ጠላቶቻቸው ምድር እንድሰድዳቸው ያደረገኝን ኀጢአት ቢናዘዙ፣ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድና ስለ ኀጢአታቸው የሚገባውን ቅጣት ቢቀበሉ፣ 42.በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይሥሐቅም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ ምድሪቱንም ዐስባታለሁ። 43.ምድሪቱ እነርሱ ለቅቀዋት ስለ ሄዱ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱ በሌሉበት ጊዜም ባድማ ሆና በሰንበቷ ትደሰታለች፤ ሕጌን በማቃለላቸውና ሥርዐቴን በመናቃቸው፣ የኀጢአታቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። 44.በዚህ ሁሉ ግን ከእነርሱ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን በማፍረስ፣ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ ፈጽሜ እስካጠፋቸው ድረስ አልተዋቸውም፤ አልጸየፋቸውምም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። 45.ስለ እነርሱም ስል፣ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 46.እግዚአብሔር በራሱና በእስራኤላውያን መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ በኩል ያቆማቸው ሥርዐቶች፣ ሕጎችና ደንቦች እነዚህ ናቸው።ምዕራፍ 27
ስለ ስጦታ የወጣ ሕግ
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ማንኛውም ሰው ተመጣጣኙን ዋጋ በመክፈል ለእግዚአብሔር ሰውን ለመስጠት የተለየ ስእለት ቢሳል፣ 3.ዕድሜው ከሃያ እስከ ስድሳ ዓመት ለሆነ ወንድ፣ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፣ ግምቱ ዐምሳ ጥሬ ሰቅል ብር ይሁን። 4.ለሴት ከሆነ ግምቱ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5.ዕድሜው ከዐምስት እስከ ሃያ ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ሃያ ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ግምቷ ዐሥር ሰቅል ይሁን። 6.ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ ዐምስት ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐምስት ሰቅል ጥሬ ብር፣ ለሴት ከሆነ ሦስት ሰቅል ጥሬ ብር ይሁን። 7.ስድሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐሥራ ዐምስት ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ዐሥር ሰቅል ይሁን። 8.ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል። 9.“ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል። 10.ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11.እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤ 12.መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል። 13.ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት። 14.“ ‘አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ቢቀድስ፣ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን ካህኑ ዋጋውን ይተምን፤ ካህኑም የተመነው ዋጋ የጸና ይሆናል። 15.ቤቱን የቀደሰው ሰው መልሶ ሊዋጀው ከፈለገ ግን፣ የዋጋውን አንድ ዐምስተኛ በዋጋው ላይ መጨመር አለበት፤ ቤቱም ዳግመኛ የራሱ ይሆናል። 16.“ ‘አንድ ሰው ከወረሰው ርስት ላይ ለእግዚአብሔር የዕርሻ መሬት ቢቀድስ፣ ዋጋው የሚተመነው ለመሬቱ በሚያስፈልገው ዘር መጠን ይሆናል፤ ይኸውም ለአንድ ሆሜር መስፈሪያ የገብስ ዘር ዐምሳ ሰቅል ጥሬ ብር ነው። 17.ሰውየው ዕርሻውን የቀደሰው በኢዮቤልዩ ዓመት ከሆነ፣ የተወሰነው ዋጋ አይለወጥም። 18.ዕርሻውን የሚቀድሰው ከኢዮቤልዩ በኋላ ከሆነ ግን፣ ካህኑ ዋጋውን የሚተምነው እስከሚመጣው የኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባሉት ዓመታት ቍጥር ልክ ነው፤ የተተመነውም ዋጋ ይቀነሳል። 19.ዕርሻውን የቀደሰው ሰው መልሶ መዋጀት ከፈለገ፣ በዋጋው ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት፤ ከዚያ በኋላ ዕርሻው እንደ ገና የራሱ ይሆናል። 20.ዕርሻውን ባይዋጅ ወይም ለሌላ ሰው አሳልፎ ቢሸጥ፣ ከዚያ በኋላ ሊዋጀው አይችልም። 21.ዕርሻው በኢዮቤልዩ በሚለቀቅበት ጊዜ ለእግዚአብሔር እንደ ተሰጠ ዕርሻ ተቈጥሮ ቅዱስና የካህናቱ ንብረት ይሆናል። 22.“ ‘አንድ ሰው የወረሰው ርስት ያልሆነውን፣ በገንዘቡ የገዛውን የዕርሻ መሬት ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፣ 23.ካህኑ የዕርሻውን መሬት ዋጋ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ባለው ጊዜ መጠን ይተምናል፤ ሰውየው የተተመነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ አድርጎ በዚያ ዕለት ይክፈል። 24.በኢዮቤልዩ ዓመትም የዕርሻው መሬት የቀድሞው ባለርስት ለነበረው፣ ለሸጠውም ሰው ይመለሳል። 25.እያንዳንዱ ዋጋ የሚተመነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ ሆኖ አንዱ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው። 26.“ ‘የእንስሳት በኵር ቀድሞውኑ የእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ ማንም ሰው የእንስሳትን በኵር ለእግዚአብሔር መቀደስ አይችልም፤ በሬም ሆነ በግ የእግዚአብሔር ነውና። 27.እንስሳው ርኩስ ከሆነ ግን፣ ባለቤቱ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ ዐምስተኛ ጨምሮ ሊዋጀው ይችላል፤ የማይዋጀው ከሆነ ግን በተተመነው ዋጋ ይሸጥ። 28.“ ‘ነገር ግን ለእግዚአብሔር የተሰጠ፣ ማንኛውም ነገር ሰውም ሆነ እንስሳ ወይም በውርስ የተገኘ መሬት አይሸጥም፤ አይዋጅምም። ለእግዚአብሔር የተሰጠ ማንኛውም ነገር እጅግ የተቀደሰ ነውና። 29.“ ‘እንዲጠፋ የተወሰነ ማንኛውም ሰው አይዋጅም፤ መገደል አለበት። 30.“ ‘ከዕርሻ ምርትም ሆነ ከዛፍ ፍሬ፣ ማንኛውም ከምድሪቱ የሚገኝ ዐሥራት የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነው። 31.አንድ ሰው ከዐሥራቱ የትኛውንም መዋጀት ቢፈልግ፣ በዋጋው ላይ አንድ ዐምስተኛ መጨመር አለበት። 32.ከቀንድ ከብቶች፣ ከበጎችና ከፍየሎች መንጋ የሚወጣው ዐሥራት ከእረኛ በትር በታች ከሚያልፉት ዐሥረኛው እንስሳ ይሆናል፤ ይህም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 33.ሰውየው መልካም የሆነውን መልካም ካልሆነው አይለይ ወይም አይተካ፤ አንዱን በሌላው ቢተካ ግን ሁለቱም እንስሳት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ ሊዋጁም አይችሉም።’ ” 34.እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጣቸው ትእዛዞች እነዚህ ናቸው።መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 112
1.ሃሌ ሉያ።
ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔርን የሚፈራ፣
በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ፤ 2.ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤
የቅኖች ትውልድ ትባረካለች። 3.ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤
ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። 4.ቸር፣ ርኅሩኅና ጻድቅ እንደ መሆኑ፣
ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል። 5.ለጋስና ያለ ማንገራገር የሚያበድር፣
ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል። 6.ለዘላለም ከስፍራው አይናወጥምና፤
ጻድቅ ሰው ሲታወስ ይኖራል። 7.ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤
ልቡ እግዚአብሔርን በመተማመን የጸና ነው። 8.ልቡ የጸና ነው፤ አይፈራምም፤
በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል። 9.በልግስና ለድኾች ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፤
ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል። 10.ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤
ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤
የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች።
ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔርን የሚፈራ፣
በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ፤ 2.ዘሩ በምድር ላይ ኀያል ይሆናል፤
የቅኖች ትውልድ ትባረካለች። 3.ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤
ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። 4.ቸር፣ ርኅሩኅና ጻድቅ እንደ መሆኑ፣
ለቅን ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል። 5.ለጋስና ያለ ማንገራገር የሚያበድር፣
ሥራውንም በትክክል የሚያከናውን ሰው መልካም ይሆንለታል። 6.ለዘላለም ከስፍራው አይናወጥምና፤
ጻድቅ ሰው ሲታወስ ይኖራል። 7.ክፉ ወሬ አያሸብረውም፤
ልቡ እግዚአብሔርን በመተማመን የጸና ነው። 8.ልቡ የጸና ነው፤ አይፈራምም፤
በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል። 9.በልግስና ለድኾች ሰጠ፤
ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል፤
ቀንዱም በክብር ከፍ ከፍ ይላል። 10.ክፉ ሰው ይህን በማየት ይበሳጫል፤
ጥርሱን ያፋጫል፤ እየመነመነም ይጠፋል፤
የክፉዎችም ምኞት ትጠፋለች።
ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 10
ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት
1.ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ እውነተኛው አካል አይደለም፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር ያለ ማቋረጥ የሚቀርበው ተደጋጋሚ መሥዋዕት፣ ለአምልኮ የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። 2.ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር። 3.ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ 4.ምክንያቱም የኰርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም። 5.ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤“መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤
ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ 6.በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት
በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሠኘህም። 7.በዚያ ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣
አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።’ ” 8.ሕጉ ይህ እንዲደረግ ቢያዝም፣ እርሱ ግን በመጀመሪያ፣ “መሥዋዕትንና መባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ ደስም አልተሠኘህበትም” ይላል። 9.ቀጥሎም፣ “እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ። 10.በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል። 11.ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። 12.ይህኛው ካህን ግን ስለ ኀጢአት አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ 13.ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ 14.ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል። 15.መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ 16.“ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነርሱ ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤
ይላል ጌታ፤
ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤
በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።” 17.ደግሞም፣
“ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣
ከእንግዲህ አላስብም” ይላል። 18.እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም።
እስከ መጨረሻው ጸንቶ ስለ መገኘት የቀረበ ጥሪ
19.እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ 20.ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው። 21.በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣ 22.ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። 23.የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። 24.እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። 25.አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ። 26.የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆነ ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ 27.የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው። 28.የሙሴን ሕግ የናቀ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይገደል ነበር። 29.ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል? 30.“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል። 31.በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው። 32.ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን አስቡ። 33.አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋራ ዐብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል። 34.እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ። 35.ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። 36.የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ የተስፋ ቃሉን እንድትቀበሉ፣ ጸንታችሁ መቆም ያስፈልጋችኋል። 37.ምክንያቱም“ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የሚመጣው እርሱ ይመጣል፤ አይዘገይም። 38.ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤
ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣
ነፍሴ በርሱ ደስ አትሰኝም።” 39.እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም።