Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 9 · ቀን 41 (ሰኞ) 📅 Tikimt 30, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 24, 25 · መዝሙረ ዳዊት 81 · ወደ ዕብራውያን 9

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 24

በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ ዘይትና ኅብስት

24፥1-3 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥20-21
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲያበሩ ለመብራቱ የሚሆን ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው። 3.አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ታቦት መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ሥርዐት ነው። 4.በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው። 5.“የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር። 6.እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው። 7.ከኅብስቱ ጋራ የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር። 8.ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9.ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”

እግዚአብሔርን መስደብ የሚያስከትለው ቅጣት

10.እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብጻዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋራ ተጣሉ። 11.የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች። 12.የእግዚአብሔር ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት። 13.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 14.“ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው። 15.እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 16.የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን ስም ከሰደበ ይገደል። 17.“ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል። 18.የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት። 19.ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጕዳት ቢያደርስ፣ የዚያው ዐይነት ጕዳት ይፈጸምበት፤ 20.ይኸውም ስብራት በስብራት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጕዳት በርሱም ላይ ይድረስበት፤ 21.እንስሳ የገደለ ማንኛውም ሰው በገደለው ፈንታ ይተካ፤ ሰው የገደለ ግን ይገደል። 22.ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” 23.ሙሴም ይህን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ እነርሱም ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወገሩት፤ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

ምዕራፍ 25

የሰባተኛው ዓመት ዕረፍት

1.እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤ 2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራሷ የእግዚአብሔርን ሰንበት ታክብር። 3.ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ። 4.በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ። 5.ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ። 6.ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋራ ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤ 7.እንዲሁም ለቤት እንስሳትህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን።

የኢዮቤልዩ ዓመት

25፥8-38 ተጓ ምብ – ዘዳ 15፥1-11
25፥39-55 ተጓ ምብ – ዘፀ 21፥2-11፤ ዘዳ 15፥12-18
8.“ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። 9.ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ። 10.ዐምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ። 11.የኀምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ። 12.ኢዮቤልዩ ስለ ሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ። 13.“ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ። 14.“ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል። 15.ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል። 16.የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና። 17.አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 18.“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። 19.ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። 20.እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። 21.በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። 22.በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ። 23.“ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ። 24.ርስት አድርጋችሁ በምትይዙት ምድር ሁሉ መሬት የሚዋጅበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጉ። 25.“ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት። 26.ነገር ግን ሰውየው ርስቱን የሚዋጅለት ምንም ዘመድ ባይኖረውና እርሱ ራሱ መዋጀት የሚችልበትን ሀብት ቢያገኝ፣ 27.ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቍጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ። 28.ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዢው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል። 29.“ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው። 30.ሙሉው ዓመት ከማለቁ በፊት መዋጀት ካልቻለ ግን፣ ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ ያለው ቤት የገዢውና የልጅ ልጆቹ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ አይመለስለትም። 31.ቅጥር በዙሪያው ባልተሠራለት መንደር ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን እንደ ዕርሻ መሬት ተቈጥረው ሊዋጁ ይችላሉ፤ በኢዮቤልዩም ይመለሳሉ። 32.“ ‘ነገር ግን ሌዋውያን የራሳቸው በሆኑት ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ቤቶቻቸውን ምን ጊዜም የመዋጀት መብት አላቸው። 33.ሌዋውያን በከተማቸው ያለውን ቤታቸውን ቢሸጡና መዋጀት ባይችሉ፣ በኢዮቤልዩ ይመለሳል፤ በሌዋውያን ከተሞች የሚገኙ ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የሌዋውያን ንብረት ናቸውና። 34.በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት ግን አይሸጥ፤ ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው ነውና። 35.“ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደምትረዳ ርዳው። 36.ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ አትቀበለው፤ አምላክህን ፍራው። 37.ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት። 38.የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ ልሆን፣ ከግብጽ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ። 39.“ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው። 40.በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቍጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤ 41.ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ። 42.እስራኤላውያን ከግብጽ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለ ሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ። 43.በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ። 44.“ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ። 45.እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ። 46.እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኗችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው። 47.“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣ 48.ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፣ 49.አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል። 50.እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋራ በመሆን ይቍጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል። 51.ብዙ ዓመት የሚቀረው ከሆነም፣ እርሱን ለመግዛት ከተከፈለው ዋጋ ላይ በቀረው ዓመት መጠን ለሚዋጅበት መልስ ይክፈል። 52.እስከ ኢዮቤልዩ ድረስ የሚቀረው ጥቂት ዓመት ከሆነም፣ በቀረው ዓመት መጠን የሚዋጅበትን መልስ ይክፈል። 53.ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ይኑር፤ አሳዳሪውም በፊትህ በጭካኔ አይግዛው። 54.“ ‘ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ እንኳ መዋጀት ባይችል፣ እርሱና ልጆቹ በኢዮቤልዩ ዓመት በነጻ ይለቀቁ፤ 55.እስራኤላውያን ለእኔ አገልጋዮቼ ናቸውና። እነርሱ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 81

1.ለመዘምራን አለቃ፤ በጊቲትየሚዜም፣ የአሳፍ መዝሙር።
1 ብርታታችን ለሆነው አምላክ በደስታ ዘምሩ፤
ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ።
2.ዝማሬውን ጀምሩ፤ ከበሮውን ምቱ፤
በበገናና በመሰንቆ ጥዑም ዜማ አሰሙ።
3.በሙሉ ጨረቃ፣ በክብረ በዓላችን ዕለት፣
በወሩ መግቢያ፣ ጨረቃ ስትወለድ መለከት ንፉ፤
4.ይህ ለእስራኤል የተሰጠ ሥርዐት፣
የያዕቆብም አምላክ ድንጋጌ ነውና።
5.ሙሉ ለሙሉ ግብጽን ለቅቆ በወጣ ጊዜ፣
ይህን ለዮሴፍ ደነገገለት።
በማላውቀውም ቋንቋ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤
6.“ትከሻውን ከሸክም ገላገልሁት፤
እጁንም ቅርጫት ከመያዝ አሳረፍሁ።
7.በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ፤ እኔም ታደግሁህ፤
በነጐድጓድ መሰወሪያ ውስጥ መለስሁልህ፤
በመሪባ ውሃ ዘንድ ፈተንሁህ።ሴላ
8.“ሕዝቤ ሆይ፤ ሳስጠነቅቅህ ስማኝ፤
እስራኤል ሆይ፤ ምነው ብታደምጠኝ!
9.በአንተ ዘንድ ባዕድ አምላክ አይኑር፤
ለሌላም አምላክ አትስገድ።
10.ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ፣
እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤
አፍህን በሰፊው ክፈተው፤ እኔም እሞላዋለሁ።
11.“ሕዝቤ ግን አላደመጠኝም፤
እስራኤልም እጅ አልሰጥ አለኝ።
12.ስለዚህ በገዛ ዕቅዳቸው እንዲሄዱ፣
አሳልፌ ለደንዳናው ልባቸው ሰጠኋቸው።
13.“ምነው ሕዝቤ ቢያደምጠኝ ኖሮ፣
እስራኤል በመንገዴ በሄደ ኖሮ፣
14.ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባንበረከክኋቸው ነበር፤
እጄን በባላጋራዎቻቸው ላይ ባነሣሁ ነበር።
15.እግዚአብሔርን የሚጠሉ በፊቱ ይርዳሉ፤
ቅጣታቸውም እስከ ዘላለም የሚዘልቅ ነው።
16.እናንተን ግን ምርጡን ስንዴ አበላችኋለሁ፤
ከዐለቱም ማር አጠግባችኋለሁ።”

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 9

በምድራዊው ድንኳን የሚደረግ አምልኮ

1.የመጀመሪያው ኪዳን የአምልኮ ሥርዐትና ምድራዊ መቅደስ ነበረው። 2.ድንኳን ተተክሎ ነበር፤ በመጀመሪያው ክፍል መቅረዙ፣ ጠረጴዛውና የመሥዋዕቱ ኅብስት ነበረበት፤ ይህም ስፍራ ቅድስት ይባላል። 3.ከሁለተኛው መጋረጃ በስተኋላ ቅድስተ ቅዱሳን የተባለ ክፍል ነበር፤ 4.በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንትና በወርቅ የተለበጠው የኪዳኑ ታቦት ነበሩ፤ ይህም ታቦት መና ያለበትን የወርቅ መሶብ፣ የለመለመችውን የአሮንን በትርና ኪዳኑ የተጻፈበትን ጽላት ይዟል። 5.በታቦቱም ላይ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ አሁን ግን ስለ እነዚህ ነገሮች በዝርዝር መናገር አንችልም። 6.ሁሉም በዚህ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ፣ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ዘወትር ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ይገባሉ። 7.ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር። 8.የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። 9.ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም። 10.እነዚህ ሁሉ እስከ መታደስ ዘመን ድረስ በምግብና በመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ በመታጠብ የሚደረጉ የሥጋ ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

የክርስቶስ ደም

11.ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ፣ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ። 12.የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ። 13.የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኰርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ 14.በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም፣ ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን! 15.ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቷልና። 16.ኑዛዜ በሚኖርበት ጊዜ የተናዛዡን ሞት ማረጋገጥ ግድ ነው፤ 17.ምክንያቱም ኑዛዜው የሚጸናው ሰውየው ሲሞት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተናዛዡ በሕይወት እስካለ ድረስ ኑዛዜው ዋጋ አይኖረውም። 18.ስለዚህ የመጀመሪያው ኪዳን እንኳ ያለ ደም የጸና አልነበረም። 19.ሙሴ እያንዳንዱን የሕግ ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ ከተናገረ በኋላ የጥጆችን ደም ከውሃ፣ ከቀይ የበግ ጠጕርና ከሂሶጵ ጋራ ወስዶ፣ በመጽሐፉና በሕዝቡ ላይ ረጨው፤ 20.እንዲህም አለ፤ “እንድትጠብቁት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው።” 21.እንዲሁም ድንኳኒቱንና ማገልገያ ዕቃውን ሁሉ በደም ረጨው። 22.በርግጥ ከጥቂት ነገሮች በቀር ሁሉም ነገር በደም መንጻት እንዳለበት ሕጉ ያዝዛል፤ ደም ሳይፈስስ ስርየት የለምና። 23.እንግዲህ የሰማያዊው ነገሮች ምሳሌ የሆኑት በእነዚህ ነገሮች ሊነጹ ግድ ነበር፤ በሰማይ ያሉት ነገሮች ግን ከዚህ በሚበልጥ መሥዋዕት ይነጻሉ። 24.ክርስቶስ የእውነተኛዪቱ ድንኳን ምሳሌ ወደ ሆነችውና በሰው እጅ ወደ ተሠራችው መቅደስ አልገባም፤ ነገር ግን አሁን ስለ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት ወደ እርሷ፣ ወደ ሰማይ ገባ። 25.ሊቀ ካህናት የራሱ ያልሆነውን ደም ይዞ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንደሚገባ፣ ክርስቶስ ራሱን ብዙ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሰማይ አልገባም። 26.እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጧል። 27.ሰው አንድ ጊዜ ሊሞት ከዚያም በኋላ በፍርድ ፊት ሊቆም ተወስኖበታል። 28.ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኗል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።