ሳምንት 10 · ቀን 49 (ሐሙስ)
📅 Hidar 10, 2019
ኦሪት ዘኍልቍ 19, 20, 21 · ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4
ኦሪት ዘኍልቍ
ምዕራፍ 19
የመንጻት ሥርዐት ውሃ
1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2.“እግዚአብሔር ያዘዘው፣ ሕጉ የሚጠይቀው ሥርዐት ይህ ነው፤ እንከን ወይም ነውር የሌለባትንና ቀንበር ተጭኖባት የማያውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡልህ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። 3.ለካህኑ ለአልዓዛርም ስጠው፤ ከሰፈሩ አውጥተውም በፊቱ ይረዷት። 4.ከዚያም ካህኑ አልዓዛር ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አቅጣጫ ሰባት ጊዜ ይርጨው። 5.እርሱ እየተመለከተም ጊደሯን ያቃጥሏት፤ ቈዳዋም፣ ሥጋዋም፣ ደሟም፣ ፈርሷም ጭምር ይቃጠል። 6.ካህኑ የዝግባ ዕንጨት፣ ሂሶጵና ብሩህ ቀይ ክር ወስዶ ጊደሯ በምትቃጠልበት እሳት ውስጥ ይጨምር። 7.ከዚህ በኋላ ካህኑ ልብሱን በውሃ ማጠብ፣ ሰውነቱንም መታጠብ አለበት፤ ከዚያም ወደ ሰፈሩ ሊመለስ ይችላል፤ ይሁን እንጂ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 8.የሚያቃጥለውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ፣ ሰውነቱንም በውሃ መታጠብ አለበት፤ እርሱም ደግሞ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል። 9.“ንጹሕ የሆነ ሰው የጊደሯን ዐመድ ዐፍሦ ከሰፈሩ ውጭ በመውሰድ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ያኑረው፤ ይህም ርኩሰትን ለሚያነጻ ውሃ እንዲውል በእስራኤል ማኅበረ ሰብ የሚጠበቅ ይሆናል፤ ከኀጢአትም ለመንጻት ይጠቅማል። 10.የጊደሯን ዐመድ የሚያፈስሰውም ሰው እንደዚሁ ልብሱን ማጠብ አለበት፤ ያም ሰው እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤላውያን እንዲሁም በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች የሚሆን ዘላለማዊ ሥርዐት ነው። 11.“የሞተን ሰው በድን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል። 12.በሦስተኛውና በሰባተኛውም ቀን ሁለመናውን በውሃው ያንጻ፤ ንጹሕም ይሆናል። በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ካላነጻ ግን ንጹሕ አይሆንም። 13.የሞተን ሰው በድን ነክቶ ራሱን ያላነጻ ማንኛውም ሰው የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያም ሰው ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ። የሚያነጻው ውሃ ስላልተረጨበት ርኩስ ነው፤ ከርኩሰቱም አልተላቀቀም። 14.“አንድ ሰው በድንኳን ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ የሚፈጸመው ሥርዐት የሚከተለው ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባም ሆነ በዚያ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል፤ 15.እንዲሁም ተከድኖ ያልታሰረ ማንኛውም ክፍት ዕቃ የረከሰ ይሆናል። 16.“ሜዳ ላይ በሰይፍ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ወይም ደግሞ ዐፅም ወይም መቃብር የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰ ይሆናል። 17.“ለረከሰውም ሰው፣ ለማንጻት ከተቃጠለው የጊደር ዐመድ ላይ ማሰሮ ውስጥ በማድረግ በላዩ የምንጭ ውሃ ይጨምሩበት። 18.ከዚያም በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ሰው ሂሶጵ ወስዶ በውሃው ውስጥ ከነከረው በኋላ ድንኳኑን፣ በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፣ እዚያ የነበሩትንም ሰዎች ሁሉ ይርጫቸው። እንዲሁም የሰው ዐፅም ወይም መቃብር ወይም ደግሞ የተገደለውን ወይም እንዲሁ የሞተውን ሰው የነካው ማንኛውንም ሰው ይርጭ። 19.የነጻው ሰው ያልነጻውን ሰው በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ይርጨው፤ በሰባተኛው ቀን ያንጻው፤ የሚነጻውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ ማምሻውም ላይ የነጻ ይሆናል። 20.ይሁን እንጂ አንድ የረከሰ ሰው ራሱን ሳያነጻ ከቀረ የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሷልና ከማኅበረ ሰቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ የሚያነጻው ውሃ ያልተረጨበት ስለ ሆነ ርኩስ ነው። 21.ይህም ለእነርሱ የዘላለም ሥርዐት ነው።“የሚያነጻውን ውሃ የሚረጨውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ የሚያነጻውንም ውሃ የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል። 22.የረከሰ ሰው የሚነካው ማንኛውም ነገር ይረክሳል፤ ይህን የነካ ሰው ደግሞ እስከ ማምሻው ድረስ የረከሰ ይሆናል።”
ምዕራፍ 20
ከዐለት የፈለቀ ውሃ
1.በመጀመሪያው ወር መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ወደ ጺን ምድረ በዳ መጥተው በቃዴስ ተቀመጡ፤ እዚያ ማርያም ሞተች፤ ተቀበረችም። 2.በዚህ ጊዜ ለማኅበረ ሰቡ የሚሆን ውሃ አልነበረም፤ ሕዝቡም ሙሴንና አሮንን በመቃወም ተሰበሰቡ። 3.ሙሴን ተጣሉት፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ ምነው እኛም ያኔ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 4.የእግዚአብሔርን ማኅበረ ሰብ ወደዚህ ምድረ በዳ ያመጣችሁት ለምንድን ነው! ከነከብቶቻችን እዚሁ እንድናልቅ ነውን? 5.ከግብጽ አውጥታችሁ እህል ወይም በለስ፣ ወይን ወይም ሮማን ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ቦታ ያመጣችሁንስ ለምንድን ነው? የሚጠጣ ውሃ እንኳ ይታጣ!” 6.ሙሴና አሮን ከማኅበረ ሰቡ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው በግንባራቸው ተደፉ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 8.“በትሪቱን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን በአንድነት ሰብስቡ፤ እነርሱም እያዩ ዐለቱን ተናገሩት፤ ዐለቱም ውሃ ያወጣል። አንተም ለማኅበረ ሰቡ ከዐለቱ ውሃ ታወጣላቸዋለህ፤ እነርሱና ከብቶቻቸውም ይጠጣሉ።” 9.ስለዚህም ሙሴ ልክ እንደ ታዘዘው በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። 10.እርሱና አሮንም ማኅበሩን በዐለቱ ፊት አንድ ላይ ሰበሰቡ፤ ሙሴም፣ “እናንተ ዐመፀኞች ስሙ፤ ከዚህ ዐለት እኛ ለእናንተ ውሃ ማውጣት አለብን?” አላቸው። 11.ከዚያም ሙሴ እጁን ዘርግቶ በበትሩ ዐለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ውሃውም ተንዶለዶለ፤ ማኅበረ ሰቡና ከብቶቻቸውም ጠጡ። 12.ነገር ግን እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፣ “በእስራኤላውያን ፊት እኔን ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ስላልታመናችሁብኝ ይህን ማኅበረ ሰብ ወደምሰጠው ምድር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው። 13.እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋራ የተጣሉበት፣ እርሱም ቅዱስ መሆኑን በመካከላቸው የገለጠበት ይህ የመሪባ ውሃ ነበር።ኤዶም እስራኤል እንዳያልፍ ከለከለ
14.ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤“ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደ ሆነ አንተም ታውቃለህ። 15.የቀድሞ አባቶቻችን ወደ ግብጽ ወረዱ፤ እኛም እዚያ ብዙ ዘመን ኖርን። ግብጻውያን እኛንም አባቶቻችንንም አሠቃዩን፤ 16.ወደ እግዚአብሔር በጮኽን ጊዜ ግን ጩኸታችንን ሰማ፤ መልአክ ልኮም ከግብጽ አወጣን።
“አሁንም ያለነው እዚሁ ቃዴስ በግዛትህ ድንበር ላይ ባለችው ከተማ ነው። 17.ስለዚህ በአገርህ እንድናልፍ እባክህን ፍቀድልን፤ በየትኛውም ዕርሻ ወይም የወይን ተክል ውስጥ አንገባም፤ ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። የንጉሡን አውራ ጐዳና ይዘን ከመጓዝ በቀር፣ ግዛትህን ዐልፈን እስክንሄድ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።” 18.ኤዶም ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤
“በዚህ በኩል አታልፉም፤ እናልፋለን የምትሉ ከሆነ በሰልፍ ወጥተን በሰይፍ እንመታችኋለን።” 19.እስራኤላውያንም መልሰው፣
“አውራውን መንገድ ይዘን እንሄዳለን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን የትኛውንም ውሃችሁን ከጠጣን ዋጋውን እንከፍላለን፤ በእግር ዐልፈን መሄድ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አንፈልግም።” አሏቸው። 20.ኤዶምም እንደ ገና፣
“በዚህ ማለፍ አትችሉም” የሚል መልስ ሰጣቸው።
ከዚያም ኤዶም ብዙና ኀይለኛ የሆነ ሰራዊት አሰልፎ ሊወጋቸው ወጣ፤ 21.ስለዚህ ኤዶም በግዛቱ ዐልፈው እንዳይሄዱ ስለ ከለከላቸው እስራኤላውያን ተመለሱ።
የአሮን መሞት
22.መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ከቃዴስ ተነሥቶ ወደ ሖር ተራራ መጣ። 23.እግዚአብሔርም በኤዶም ወሰን አጠገብ ባለው በሖር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 24.“አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል፤ ሁለታችሁም በመሪባ ውሃ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችኋልና ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም። 25.አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ወደ ሖር ተራራ ይዘሃቸው ውጣ። 26.አሮን ወደ ወገኖቹ ስለሚሰበሰብ ልብሱን አውልቀህ ልጁን አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም እዚያው ይሞታል።” 27.ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ መላው ማኅበረ ሰብ እያያቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ። 28.ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም እዚያው ተራራው ጫፍ ላይ ሞተ። ከዚያም ሙሴና አልዓዛር ከተራራው ወረዱ፤ 29.መላው ማኅበረ ሰብም አሮን መሞቱን በተረዳ ጊዜ፣ የእስራኤል ቤት በሙሉ ሠላሳ ቀን አለቀሰለት።ምዕራፍ 21
የዓራድ መደምሰስ
1.በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። 2.በዚያ ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ። 3.እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ።ከናስ የተሠራው እባብ
4.እስራኤላውያን በኤዶም ዞረው ለመሄድ ስላሰቡ ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ በመንገድ ሳለ ትዕግሥቱ ዐለቀ፤ 5.በእግዚአብሔርና በሙሴም ላይ ተነሥተው፣ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብጽ ያወጣችሁን ለምንድን ነው? ምግብ የለ! ውሃ የለ! ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” ሲሉ ተናገሩ። 6.በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መርዘኛ እባቦች ሰደደባቸው፤ ሕዝቡን ነደፉ፤ ብዙ እስራኤላውያንም ሞቱ። 7.ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። 8.እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እባብ ሠርተህ በዕንጨት ላይ ስቀለው፤ የተነደፈውም ሁሉ ወደ እርሱ በማየት ይድናል” አለው። 9.ስለዚህ ሙሴ የናስ እባብ ሠርቶ በዕንጨት ላይ ሰቀለ፤ ከዚያም በእባብ የተነደፈ ማንኛውም ሰው ወደ ናሱ እባብ በተመለከተ ጊዜ ይድን ነበር።ወደ ሞዓብ የተደረገው ጕዞ
10.እስራኤላውያን ተጓዙ፤ በአቦትም ሰፈሩ፤ 11.ከዚያም ከአቦት ተነሥተው፣ በፀሓይ መውጫ ትይዩ ባለው የሞዓብ ምድረ በዳ በዒዮዓባሪም ሰፈሩ። 12.ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13.ከዚያም ተነሥተው እስከ አሞራውያን ግዛት በሚዘልቀው ምድረ በዳ ባለው በአርኖን አጠገብ ሰፈሩ፤ አርኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል የሚገኝ የሞዓብ ወሰን ነው። 14.እንግዲህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በዚሁ የተነሣ ነው፤“…በሱፋ ውስጥ የሚገኘው ዋሄብ
አርኖንና 15.ወደ ዔር የሚወስዱት
በሞዓብ ድንበርም የሚገኙት
የሸለቆች ተረተሮች።” 16.ከዚያም እግዚአብሔር ለሙሴ፣ “ሰዎቹን በአንድነት ሰብስባቸውና ውሃ እሰጣቸዋለሁ” ወዳለበት ብኤር ወደተባለው የውሃ ጕድጓድ ጕዟቸውን ቀጠሉ። 17.ከዚያም እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ፤
“አንተ ምንጭ ሆይ ፍለቅ!
እናንተም ዘምሩለት፤ 18.ልዑላን ለቈፈሩት፣
የሕዝብ አለቆች በበትረ መንግሥታቸውና በበትሮቻቸው ላጐደጐዱት፣
የውሃ ጕድጓድ ዘምሩለት።”
ከዚህ በኋላ ከምድረ በዳው ወደ መቴና ሄዱ፤ 19.ከመቴና ወደ ነሃሊኤል፣ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፣ 20.ከባሞትም ፈስጋ ላይ ሆኖ ምድረ በዳው ቍልቍል ወደሚታይበት በሞዓብ ወደሚገኘው ሸለቆ ተጓዙ።
የሴዎንና የዐግ ድል መሆን
21.እስራኤል ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን እንዲህ የሚሉ መልእክተኞች ላከ፤ 22.“አገርህን አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ወደ የትኛውም ዕርሻ ሆነ የወይን አትክልት አንገባም፤ ወይም ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። ከግዛትህ እስክንወጣ ድረስም የንጉሡን አውራ ጐዳና አንለቅም።” 23.ሴዎን ግን እስራኤል በግዛቱ ውስጥ እንዲያልፍ አልፈቀደም፤ ሰራዊቱን በሙሉ አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ ምድረ በዳው ወጣ፤ ያሀጽ እንደ ደረሰም ከእስራኤል ጋራ ጦርነት ገጠመ። 24.እስራኤል ግን በሰይፍ መታው፤ ከአርኖን እስከ ያቦቅ ድረስ ያለውንም ምድሩን ወሰደበት፤ ይሁን እንጂ የአሞናውያን ወሰን የተመሸገ ስለ ነበር ከያቦቅ አላለፈም። 25.እስራኤልም ሐሴቦንና በአካባቢዋ ያሉትን ከተሞቹን ጨምሮ የአሞራውያንን ከተሞች በሙሉ በመያዝ እዚያው ተቀመጠ። 26.ሐሴቦን የቀድሞውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ያለውን ምድሩን የወሰደበት የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረች። 27.እንግዲህ ባለቅኔዎች እንደዚህ ያሉት ለዚህ ነው፤“ወደ ሐሴቦን ኑ፣ እንደ ገና ትገንባ፤
የሴዎንም ከተማ ተመልሳ ትሠራ። 28.“እሳት ከሐሴቦን ወጣ፤
ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ተንቦገቦገ፤
የሞዓብን ዔር፣
በአርኖን ከፍታዎች የሚኖሩትንም አለቆች በላ። 29.ሞዓብ ሆይ፤ ወዮልህ!
የካሞሽ ሕዝብ ሆይ፤ ተደመሰስህ!
ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፣
ሴቶች ልጆቹን ለምርኮ፣
ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን አሳልፎ ሰጥቷል። 30.“እኛ ግን ገለበጥናቸው፤
ሐሴቦን እስከ ዲቦን ድረስ ተደመሰሰች፤
እስከ ኖፋ ድረስ ያሉትን፣
እስከ ሜድባ የተዘረጉትን እንዳሉ አፈራርሰናቸዋል።” 31.ስለዚህም እስራኤል በአሞራውያን ምድር ተቀመጠ። 32.ሙሴ ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ከላከ በኋላ እስራኤላውያን በአካባቢዋ ያሉትን መንደሮች በመያዝ እዚያ የነበሩትን አሞራውያን አባረሯቸው። 33.ከዚያም ተመልሰው ወደ ባሳን የሚወስደውን መንገድ በመያዝ ሄዱ፤ የባሳን ንጉሥ ዐግና መላ ሰራዊቱም ኤድራይ ላይ ጦርነት ሊገጥሟቸው ወጡ። 34.እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እርሱን ከመላው ሰራዊቱና ከምድሩ ጋራ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና አትፍራው። በሐሴቦን ሆኖ ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን ሁሉ በርሱም ላይ አድርግበት” አለው። 35.ስለዚህም እስራኤላውያን ዐግን ከልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋራ አንድም ሳይቀሩ ሁሉንም አጠፏቸው፤ ምድሩንም ወረሱ።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች
ምዕራፍ 4
1.ጌቶች ሆይ፤ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ስለምታውቁ ባሮቻችሁን በፍትሕና በቅንነት አስተዳድሯቸው።