ሳምንት 10 · ቀን 47 (ማክሰኞ)
📅 Hidar 8, 2019
ኦሪት ዘኍልቍ 12, 13, 14 · መዝሙረ ዳዊት 28 · ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2
ኦሪት ዘኍልቍ
ምዕራፍ 12
ማርያምና አሮን ሙሴን ተቃወሙ
1.ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት አግብቶ ነበርና ባገባት ኢትዮጵያዊት ምክንያት ማርያምና አሮን ይነቅፉት ጀመር። 2.እነርሱም፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አልተናገረም?” ተባባሉ፤ እግዚአብሔርም ይህን ሰማ። 3.ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር። 4.ወዲያው እግዚአብሔር ሙሴን፣ አሮንንና ማርያምን፣ “ሦስታችሁም ውጡና ወደ መገናኛው ድንኳን ኑ” አላቸው፤ ሦስቱም ወጥተው ሄዱ። 5.ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ዐምድ ወረደ፤ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፣ 6.እንዲህ አላቸው፤ “ቃሌን ስሙ፤“የእግዚአብሔር ነቢይ በመካከላችሁ ቢኖር፣
በራእይ እገለጥለታለሁ፤
በሕልምም እናገረዋለሁ። 7.ለአገልጋዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤
እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። 8.እኔ ከርሱ ጋራ የምነጋገረው ፊት ለፊት ነው፤
በግልጽ እንጂ በልዩ ዘይቤ አይደለም፤
እርሱ የእግዚአብሔርን መልክ ያያል።
ታዲያ እናንተ አገልጋዬን ሙሴን
ትቃወሙ ዘንድ ለምን አልፈራችሁም?” 9.የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እርሱም ትቷቸው ሄደ። 10.ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ ጊዜ፣ እነሆ፤ ማርያም በለምጽ ተመታች፤ እንደ በረዶም ነጣች። አሮንም ወደ እርሷ ዘወር ሲል ለምጽ ወርሷት አየ፤ 11.ሙሴንም እንዲህ አለው፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በስንፍናችን የሠራነውን ኀጢአት እባክህ አትቍጠርብን። 12.እርሷንም በእናቱ ማሕፀን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋላ የተወለደ ጭንጋፍ መስላ እንድትቀር አታድርግ።” 13.ስለዚህም ሙሴ፣ “አምላክ ሆይ፤ እባክህ ፈውሳት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 14.እግዚአብሔርም ለሙሴ፣ “አባቷ እፊቷ ላይ ቢተፋባት እስከ ሰባት ቀን በኀፍረት መቈየት አይገባትምን? አሁንም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን እንድትገለል አድርግ፤ ከዚያ በኋላ ግን ልትመለስ ትችላለች” ሲል መለሰለት። 15.ስለዚህም ማርያም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተገለለች፤ ከዚያ እስክትመለስም ሕዝቡ ጕዞውን አልቀጠለም ነበር። 16.ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተነሣ፤ በፋራን ምድረ በዳም ሰፈረ።
ምዕራፍ 13
ከነዓንን መሰለል
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለእስራኤላውያን የምሰጠውን የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ ጥቂት ሰዎች ላክ፤ ከእያንዳንዱም የአባቶች ነገድ አለቃ ይላክ።” 3.ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ እነዚህን ላካቸው፤ ሁሉም የእስራኤላውያን አለቆች ነበሩ። 4.ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፤ከሮቤል ነገድ፣ የዛኩር ልጅ ሳሙኤል፤ 5.ከስምዖን ነገድ፣ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤ 6.ከይሁዳ ነገድ፣ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤ 7.ከይሳኮር ነገድ፣ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤ 8.ከኤፍሬም ነገድ፣ የነዌ ልጅ አውሴ፤ 9.ከብንያም ነገድ፣ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ 10.ከዛብሎን ነገድ፣ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤ 11.ከምናሴ ነገድ ይህም የዮሴፍ ነገድ ነው፤ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤ 12.ከዳን ነገድ፣ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤ 13.ከአሴር ነገድ፣ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤ 14.ከንፍታሌም ነገድ፣ የያቢ ልጅ ናቢ፤ 15.ከጋድ ነገድ፣ የማኪ ልጅ ጉዲኤል። 16.እንግዲህ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴ ለነዌ ልጅ ለአውሴ፣ “ኢያሱ” የሚል ስም አወጣለት። 17.ሙሴም ከነዓንን እንዲሰልሉ በላካቸው ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ኔጌብን ዘልቃችሁ ወደ ተራራማው አገር ግቡ። 18.ምድሪቱ ምን እንደምትመስልና የሚኖሩባትም ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፣ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች መሆናቸውን እዩ። 19.የሚኖሩባት ምድር ምን ዐይነት ናት? መልካም ወይስ መጥፎ? የሚኖሩባቸውስ ከተሞች ምን ይመስላሉ? በግንብ ያልታጠሩ ናቸው ወይስ የተመሸጉ? 20.ዐፈሩስ እንዴት ያለ ነው? ለም ወይስ ደረቅ? ደናም ወይስ ደን አልቦ? በተቻለ መጠን ከምድሪቱ በኵር ፍሬ ይዛችሁ ኑ።” ወቅቱ የወይን ፍሬ መብሰል የጀመረበት ጊዜ ነበር። 21.ስለዚህ ወጥተው ከጺን ምድረ በዳ አንሥቶ በሌቦ ሐማት በኩል እስከ ረአብ ድረስ ዘልቀው ምድሪቱን አጠኑ። 22.በኔጌብ በኩል ዐልፈው አኪመን፣ ሴሲና ተላሚ የተባሉ የዔናቅ ዝርያዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን መጡ። ኬብሮን የተመሠረተችው ጣኔዎስ በግብጽ ምድር ከመቈርቈሯ ሰባት ዓመት አስቀድሞ ነበር። 23.ወደ ኤሽኮል ሸለቆ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላ ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ይህንም ከሮማንና ከበለስ ጋራ በመሎጊያ አድርገው ለሁለት ተሸከሙት። 24.እስራኤላውያን የወይን ዘለላ ስለ ቈረጡባትም ያች ስፍራ የኤሽኮል ሸለቆ ተባለች። 25.ምድሪቱንም ዐሥሠው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።
ሰላዮቹ ያቀረቡት የዐሠሣ ውጤት
26.ሰዎቹም፣ ሙሴና አሮን መላውም የእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ወዳሉበት በፋራን ምድረ በዳ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተመለሱ፤ ያዩትንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ አስረዱ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው። 27.ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “ወደ ላክኸን ምድር ዘልቀን ገባን፤ ማርና ወተት የምታፈስስ ናት፤ ፍሬዋም ይኸው። 28.በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ግን ኀያላን ሲሆኑ፣ ከተሞቹም የተመሸጉና ትላልቅ ናቸው፤ እንዲያውም የዔናቅን ዝርያዎች በዚያ አይተናል። 29.አማሌቃውያን የሚኖሩት በኔጌብ፣ ኬጢያውያን ኢያቡሳውያንና አሞራውያን በኰረብታማው አገር፣ ከነዓናውያን የሚኖሩት ደግሞ በባሕሩ አቅራቢያና በዮርዳኖስ ዳርቻ ነው።” 30.ከዚያም ካሌብ ሕዝቡን በሙሴ ፊት ጸጥ አሠኝቶ፣ “እንውጣ! ምድራቸውን እንውረስ፤ ማሸነፍም እንችላለን” አላቸው። 31.ከእነርሱ ጋራ የወጡት ሰዎች ግን፣ “ከእኛ ይልቅ ብርቱዎች ስለ ሆኑ፣ ልናሸንፋቸው አንችልም” አሉ። 32.እነዚህም ስለ ሰለሏት ምድር በእስራኤላውያን መካከል እንዲህ የሚል መጥፎ ወሬ አሠራጩ፤ “ያየናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ናት፤ እዚያ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ግዙፎች ናቸው፤ 33.ኔፊሊምንም በዚያ አይተናል፤ የዔናቅ ዝርያዎች የመጡት ከኔፊሊም ነው። ራሳችንን ስናየው እንደ አንበጣ ነበርን፤ በእነርሱ ዐይን የታየነውም በዚሁ መልክ ነበር።”ምዕራፍ 14
የሕዝቡ ማመፅ
1.በዚያች ሌሊት ማኅበረ ሰቡ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸና አለቀሰ። 2.እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አሏቸው፤ “ምነው በግብጽ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! 3.እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር የሚያመጣን ለምንድን ነው? በሰይፍ እንድንወድቅ ነውን? ሚስቶቻችንና ልጆቻችንም ይማረካሉ፤ ታዲያ ወደ ግብጽ መመለሱ አይሻለንም?” 4.እርስ በርሳቸውም፣ “አለቃ መርጠን ወደ ግብጽ እንመለስ” ተባባሉ። 5.ከዚያም ሙሴና አሮን እዚያ በተሰበሰቡት በመላው እስራኤላውያን ማኅበር ፊት በግንባራቸው ተደፉ። 6.ምድሪቱን ከሰለሏት መካከል የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7.ለመላው የእስራኤል ማኅበርም እንዲህ አሉ፤ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። 8.እግዚአብሔር በእኛ ደስ ከተሠኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል። 9.ብቻ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሯቸው። ጥላቸው ተገፍፏል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋራ ነውና አትፍሯቸው።” 10.መላው ማኅበር ግን በድንጋይ ሊወግሯቸው ተነጋገሩ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ክብር በመገናኛው ድንኳን ለእስራኤላውያን ሁሉ ተገለጠ። 11.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ እስከ መቼ ይንቀኛል? እነዚህን ሁሉ ታምራት በመካከሉ እያደረግሁ የማያምንብኝስ እስከ መቼ ነው? 12.በቸነፈር እመታዋለሁ፤ እደመስሰዋለሁም፤ አንተን ግን ብርቱና ታላቅ ለሆነ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 13.ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ነገሩን ግብጻውያን ቢሰሙትስ! ይህን ሕዝብ በኀይልህ ከመካከላቸው አውጥተኸዋልና፤ 14.የተደረገውንም በዚች ምድር ለሚኖሩት ሰዎች ይነግሯቸዋል። እግዚአብሔር ሆይ፣ አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋራ መሆንህን፣ ደግሞም አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊት ለፊት እንደ ታየህና ደመናህ በላያቸው እንደ ሆነ፣ አንተም ቀን በደመና ዐምድ ሌሊትም በእሳት ዐምድ እፊት እፊታቸው እየሄድህ እንደ መራሃቸው ቀድሞውኑ ሰምተዋል። 15.ታዲያ ይህን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ጊዜ ብትፈጀው ዝናህን የሰሙ ሕዝቦች፣ 16.‘እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ ይሰጠው ዘንድ በመሐላ ቃል ወደ ገባለት ምድር ሊያስገባው ባለመቻሉ በምድረ በዳ ፈጀው’ ይሉሃል። 17.“አሁንም እንዲህ ስትል በተናገርኸው መሠረት የጌታ ኀይል ይገለጥ፤ 18.‘እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩ የበዛ፣ ኀጢአትንና ዐመፃን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ የማይተው፣ ስለ አባቶቻቸውም ኀጢአት ልጆችን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ የሚቀጣ ነው።’ 19.ከግብጽ ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው ሁሉ እንደ ፍቅርህ ታላቅነት መጠን እባክህ አሁንም የዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።” 20.እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “በጠየቅኸው መሠረት ይቅር ብያቸዋለሁ፤ 21.ይሁን እንጂ ሕያው እንደ መሆኔና የእግዚአብሔርም ክብር ምድርን ሁሉ የሞላ እንደ መሆኑ መጠን፣ 22.ክብሬን ደግሞም በግብጽና በምድረ በዳ ያደረግኋቸውን ታምራት አይተው ካልታዘዙኝና ዐሥር ጊዜ ከተፈታተኑኝ ሰዎች አንዳቸውም፣ 23.ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም። የናቀኝ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ አያያትም፤ 24.አገልጋዬ ካሌብ ግን የተለየ መንፈስ ስላለውና በፍጹም ልቡ የተከተለኝ በመሆኑ ሄዶባት ወደ ነበረችው ምድር አስገባዋለሁ፤ ዘሮቹም ይወርሷታል። 25.አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በሸለቆው የሚኖሩ ስለ ሆነ በነገው ዕለት ተመልሳችሁ በቀይ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳው ሂዱ።” 26.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 27.“ይህ ክፉ ማኅበረ ሰብ በእኔ ላይ የሚያጕረመርመው እስከ መቼ ነው? የእነዚህን ነጭናጮች እስራኤላውያን ማጕረምረም ሰምቻለሁ። 28.ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሕያው ነኝ፤ ስትናገሩ የሰማኋችሁን እነዚያን ነገሮች አደርግባችኋለሁ፤ 29.በተደረገው ቈጠራ መሠረት፣ ሃያ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆናችሁና በእኔም ላይ ያጕረመረማችሁ ሁሉ በድናችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃል። 30.መኖሪያችሁ እንድትሆን በጽኑ ወደማልሁላችሁ ምድር ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእናንተ አንዳችሁም አትገቡባትም። 31.ይማረካሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን ግን አገባቸዋለሁ፤ እናንተ የናቃችኋትን ምድር እነርሱ ይደሰቱባታል። 32.እናንተ ግን፣ በድናችሁ በዚሁ ምድረ በዳ ወድቆ ይቀራል። 33.ካለማመናችሁ የተነሣ ከእናንተ የመጨረሻው በድን እዚሁ ምድረ በዳ እስኪወድቅ ድረስ፣ ልጆቻችሁ መከራ እየበሉ አርባ ዓመት እረኞች ይሆናሉ። 34.ምድሪቱን ለመሰለል በቈያችሁበት አርባ ቀን ልክ እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት ተቈጥሮ ስለ ኀጢአታችሁ አርባ ዓመት መከራ ትቀበላላችሁ፤ ምን ያህል በእናንተ ላይ እንደ ተነሣሁም ታውቃላችሁ።’ 35.እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም አንድ ሆኖ በተነሣብኝ በዚህ ክፉ ማኅበረ ሰብ ሁሉ ላይ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ፤ መጨረሻቸው በዚሁ ምድረ በዳ ይሆናል፤ እዚሁም ይሞታሉ።” 36.ከዚህ በኋላ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሙሴ ልኳቸው የነበሩትና ከዚያ ተመልሰው ስለ ምድሪቱ ክፉ ወሬ በማሠራጨት ማኅበረ ሰቡ በሙሉ እንዲያጕረመርሙበት ያደረጉ፣ 37.ስለ ምድሪቱም ክፉ ወሬ በማሠራጨት ተጠያቂ የሆኑት እነዚሁ ሰዎች ተቀሥፈው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ። 38.ምድሪቱን እንዲሰልሉ ከተላኩት ሰዎች በሕይወት የተረፉት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ብቻ ነበሩ። 39.ሙሴም ይህን ለእስራኤላውያን ሁሉ በነገራቸው ጊዜ ክፉኛ ዐዘኑ። 40.በማግስቱም ጧት ማልደው ወደ ተራራማው አገር ወጡ፤ እንዲህም አሉ፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጠን ስፍራ እንወጣለን”። 41.ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትጥሳላችሁ? ይህም አይሳካላችሁም! 42.እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ስላይደለ አትውጡ፤ በጠላቶቻችሁ ድል ትነሣላችሁ፤ 43.አማሌቃውያንና ከነዓናውያን በዚያ ያጋጥሟችኋልና። እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁትና እርሱም ከእናንተ ጋራ ስለማይሆን በሰይፍ ትወድቃላችሁ።” 44.ሙሴም ሆነ የእግዚአብሔር ታቦት ቃል ኪዳን ከሰፈር ሳይነሡ በስሜት ተገፋፍተው ብቻ ወደ ተራራማው አገር ወጡ። 45.በዚህ ጊዜ በተራራማው አገር የሚኖሩት አማሌቃውያንና ከነዓናውያን ወርደው ወጓቸው፤ እስከ ሖርማ ድረስም አሳደዷቸው።መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 28
1.የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤
ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤
አንተ ዝም ካልኸኝ፤
ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ። 2.ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣
እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣
የልመናዬን ቃል ስማ። 3.በልባቸው ተንኰል እያለ፣
ከባልንጀሮቻቸው ጋራ በሰላም ከሚናገሩ፣
ከክፉ አድራጊዎችና
ከዐመፃ ሰዎች ጋራ ጐትተህ አትውሰደኝ። 4.እንደ ሥራቸው፣
እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤
እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤
አጸፋውን መልስላቸው። 5.ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣
ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣
እርሱ ያፈርሳቸዋል፤
መልሶም አይገነባቸውም። 6.የልመናዬን ቃል ሰምቷልና፣
እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። 7.እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤
ልቤ በርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤
ልቤ ሐሤት አደረገ፤
በዝማሬም አመሰግነዋለሁ። 8.እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤
ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው። 9.ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤
እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤
ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤
አንተ ዝም ካልኸኝ፤
ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ። 2.ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣
እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣
የልመናዬን ቃል ስማ። 3.በልባቸው ተንኰል እያለ፣
ከባልንጀሮቻቸው ጋራ በሰላም ከሚናገሩ፣
ከክፉ አድራጊዎችና
ከዐመፃ ሰዎች ጋራ ጐትተህ አትውሰደኝ። 4.እንደ ሥራቸው፣
እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤
እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤
አጸፋውን መልስላቸው። 5.ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣
ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣
እርሱ ያፈርሳቸዋል፤
መልሶም አይገነባቸውም። 6.የልመናዬን ቃል ሰምቷልና፣
እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። 7.እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤
ልቤ በርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤
ልቤ ሐሤት አደረገ፤
በዝማሬም አመሰግነዋለሁ። 8.እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤
ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው። 9.ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤
እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች
ምዕራፍ 2
1.ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ስለማያውቁ ሁሉ ምን ያህል እየተጋደልሁ እንደ ሆነ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤
2.ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጽግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤
3.የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነውና።
4.ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ።
5.ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋራ ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።